ቀጥታ፡

የሀዲያ ዘመን መለወጫ በዓል ''ያሆዴ'' የአብሮነት እሴትን በማጎልበት የጋራ ትርክትን ለመገንባት ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው- ምሁራን

ሆሳዕና ፤ መስከረም 9/2019 (ኢዜአ)፡-የሀዲያ ዘመን መለወጫ በዓል ''ያሆዴ'' የአብሮነት እሴትን በማጎልበት የጋራ ትርክትን ለመገንባት ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የዋቸሞ ዩኒቨርስቲ ምሁራን ገለፁ።

የሃዲያ ዘመን መለወጫ በዓል ''ያሆዴ''ን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከበሩ የዘመን መለወጫ በዓላት ፍቅርን፣ ሰላምን፣ አብሮነትንና አንድነትን የሚያጠናክሩ የይቅርታና የመተሳሰብ በዓላት ናቸው፡፡


 

በሃዲያ ዘመን መለወጫ በዓል ''ያሆዴ'' ላይ ጥናት ያካሄዱ የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን እንደተናገሩት፤ በዓሉ የማህበረሰቡን የአንድነት እሴት በማጎልበት የጋራ ትርክትን ለመገንባት የሚያስችል እድልን የሚፈጥር ነው፡፡

በዩኒቨርሲቲው የሶሾሎጂ ትምህርት ክፍል መምህር መለሰ አቢዴ፤ የሀዲያ ዘመን መለወጫ በዓል ''ያሆዴ'' የአብሮነት እሴትን በማጎልበት ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።

በዓሉ በሃዲያ ተወላጆች ዘንድ በጉጉት የሚጠበቅና በተለያየ መንገድ ተለያይተው የቆዩ ሰዎች የሚሰባሰቡበት በዓል ስለመሆኑም ተናግረዋል።


 

በዓሉ የኢትዮጵያውያንን የኖረ የመረዳዳትና የመጠያየቅ እሴት የሚያጠናክሩ ትሩፋቶች ተግባራዊ የሚደረግበት መሆኑንም አክለዋል።

በተለያዩ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ዘንድ የሚከበሩ በዓላት የማህበረሰቡን የእርስ በእርስ ትስስር በማጠናከር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበቱ ስለመምጣታቸውም አመልክተዋል።

የ «ያሆዴ» በዓል አከባበርም የወል እሴትን ከመገንባት በተጨማሪ የኖረውን የአብሮነት እሴት በማጠናከርና የባህል፣ የታሪክና የቋንቋ ትውውቅን እያሳደገ ይገኛል ብለዋል።

የኢትዮጵያውያንን እሴቶች ጠብቆ ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ በጥናትና ምርምር የተደገፈ ማስረጃ የመሰነድ ስራ መጠናከር እንዳለበት ጠቅሰው ለዚህም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

በዩኒቨርሲቲው የሶሾሎጂ ትምህርት መምህር ታረቀኝ ንኩሮ በበኩላቸው የ ''ያሆዴ'' በዓል የመረዳዳትና የመጠያየቅ እሴትን ለማጎልበት ጉልህ ድርሻ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የ «ያሆዴ» በዓል ከልዩነት ይልቅ አብሮነትን በማፅናት ለጋራ ተጠቃሚነት መትጋትን የሚያረጋግጥ ነባር ቱባ ባህላዊ እሴት የሚንፀባረቅበት በመሆኑ ለጋራ ትርክት ግንባታ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል፡፡


 

በማህበረሰቡ መካከል ዘላቂ ሰላምን በማፅናት የመተሳሰብ ባህልን ለማጠናከር የበዓሉን ትሩፋት አስጠብቆ ለተተኪው ትውልድ ማስተላለፍ የሚያስችል በጥናት የተደገፈ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

አቅመ ደካማ ወገኖችን ከበዓሉ አስቀድሞ በመለየት ያለባቸውን ችግሮች በመቅረፍ አስፈላጊ ድጋፍ እንደሚደረግላቸውም ጠቁመዋል።

እንደ ሀዲያ ዘመን መለወጫ በዓል «ያሆዴ»ን የመሰሉ ባህላዊ እሴቶችን በመጠበቅ ማህበራዊ መስተጋብሮችን ማጎልበት ጠቃሚ መሆኑን ጠቅሰው በዓሉ በመሰባሰብ የሚከበር በመሆኑ ጥላቻንና አለመግባባትን የሚፈታ ነው ብለዋል፡፡

የሀድያ ዘመን መለወጫ በዓል «ያሆዴ» መስከረም 11 እና 12/2019 ዓ/ም በተለያዩ ባህላዊ ስነ-ስርዓቶች በደማቅ ሁኔታ ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም