ቀጥታ፡

"ጊፋታ" ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ የጋራ ሀብት በመሆኑ የመንከባከብና ጠብቆ የማቆየት ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል

ወላይታ ሶዶ፤ መስከረም 9/2018 (ኢዜአ)፦ የወላይታ ዘመን መለወጫ በዓል "ጊፋታ" ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ የጋራ ሀብት በመሆኑ የመንከባከብና ጠብቆ የማቆየት ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ገብረ መስቀል ጫላ ተናገሩ።

የወላይታ ዘመን መለወጫ በዓል "ጊፋታ" በአውደ ጥናትና በተለያዩ ዝግጅቶች በወላይታ ሶዶ ከተማ እየተከበረ ነው።


 

በአውደ ጥናቱ መድረክ ላይ የተገኙት አቶ ገብረመስቀል "ጊፋታ"ን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የተደረጉ ጥረቶች ፍሬ አፍርተው ዛሬ የዓለም ቅርስ ሆኗል ብለዋል።

"ጊፋታ" የሰላም፣ የፍቅርና የሕብረ-ብሔራዊነት መገለጫ መሆኑን ገልጸው፤ የሕዝቡን ቋንቋ፣ ባህልና ታሪክ ጠብቆ ለማቆየት በየዓመቱ የሚካሄደው አውደ ጥናት ትልቅ ድርሻ መወጣቱን አስረድተዋል።

ወላይታ በርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሱ ቅርሶች ባለቤት መሆኑን አንስተው ከእነዚህም መካከል "ጊፋታ" የተራራቁ የሚቀራረቡበትና የተጣሉ ታርቀው ፍቅር የሚያበስሩበት ልዩ በዓል ነው ብለዋል።

"ጊፋታ" ዛሬ ተከብሮ የሚቀር ሳይሆን ነገም የሚቀጥል ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ የጋራ ሀብት በመሆኑ መንከባከብና ጠብቆ የማቆየት ኃላፊነት መወጣት ያስፈልጋል ሲሉም አሳስበዋል።


 

የ2019 ዓ.ም የ"ጊፋታ" በዓል በዩኔስኮ በሰው ልጅ ወካይ ቅርስነት በተመዘገበበት ማግስት የሚከበር መሆኑ የዘንድሮውን የጊፋታ በዓል አከባበር ልዩ ያደርገዋል ያሉት ደግሞ የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ ናቸው።

"ጊፋታ" ቂምና ቁርሾን በማስወገድ፣ መገፋፋትንና መጠፋፋትን በማውገዝ፣ ሰላም፣ መቻቻልንና መተጋገዝን መሠረት ያደረገ በዓል መሆኑንም ገልጸዋል።

በዓሉ በሀገር ውስጥና በውጭ በተለያዩ አካባቢዎች እንደሚከበር ጠቅሰው፣ እሴቶቹ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማሻገር ሁሉም የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት እንዳለበትም አሳስበዋል።

የዞኑ ባህልና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ስምኦን ስላሎ በበኩላቸው ዕለቱ የሕዝቡ ቋንቋ፣ ባህልና ታሪክ ተጠብቆ እንዲቆይ በትኩረት የምንመክርበት ነው ብለዋል።

መምሪያው በዓሉ ተጠብቆ እንዲቆይ ግብ ጥሎ ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመው የወላይታ ቋንቋ፣ ባህልና ታሪክ በዓለም ሕዝብ ዘንድ የተሻለ ትኩረት እንዲያገኝ የተጀመሩ ተግባራት ይጠናከራሉ ብለዋል።

በመድረኩ የፌዴራል፣ የክልልና የዞን እንዲሁም የከተማ አስተዳደር የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም