በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በቅንጅት የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል-የሰላም ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በቅንጅት የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል-የሰላም ሚኒስቴር
ባሕርዳር፤ መስከረም 9/2019 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሃገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ሴቶችና ወጣቶች ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመቀናጀት የሚያከናውኗቸው ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የሰላም ሚኒስቴር አመለከተ።
የሰላም ሚኒስቴር ከአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
የሰላም ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ኃላፊና የሚኒስትሩ ተወካይ አቶ መብራቱ ካሳ በመድረኩ እንደገለፁት፤ኢትዮጵያ በተለያየ ወቅት የገጠሟትን ፈተናዎች በፅናት እየተወጣች ትገኛለች።
በተለይ በአማራ ክልል አጋጥሞ የነበረውን የሰላም እጦት መላ ህዝቡ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ ሴቶችና ወጣቶች ከፀጥታ ኃይሉ ጋር ተቀናጅተው በከፈሉት ዋጋ በክልሉ ዘላቂ ሰላም እየተረጋገጠ እንዲመጣ መሰረት መጣሉን ገልፀዋል።
የመድረኩ አላማም በክልሉ እየተረጋገጠ የመጣውን ሰላም በቀጣይም በዘላቂነት አጠናክሮ ለማስቀጠል ያለመ መሆኑን አብራርተዋል።
የፀጥታ ኃይሉ፣ ወጣቶችና ሴቶች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎችና ሌሎች በጋራ ያመጡትን ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል የጀመሩትን ሰላምን የማፅናት ተግባር አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም አሳስበዋል።
የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ/ር) በበኩላቸው በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በተደረገ የጋራ ጥረት ሰላሙ እየተረጋገጠ መምጣቱን ገልፀዋል።
በተለይ ታሪካዊ ጠላቶቻችንና ፅንፈኛ ኃይሎች ክልሉንና ኢትዮጵያን ለመበተን ያደረጉትን ጥረት በፀጥታ ኃይሉና በህዝቡ የጋራ ቅንጅት ማክሸፍ መቻሉን ተናግረዋል።
ሰላም ለሰው ልጆች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረት ነው ያሉት እሸቱ (ዶ/ር) ሰላምን ማጽናት ለመንግስትና ለፀጥታ ተቋማት ብቻ የሚተው ሳይሆን ሁላችንም በጋራ የምናረጋግጠው ተግባር መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም የክልሉን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ የህይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ እናቶች ፣ሴቶችና ወጣቶች፣ ከመንግስትና ከፀጥታ ኃይሉ ጋር የጀመሩትን ሰላም የማረጋገጥ ስራ አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።
ሰላም የሚገነባው በጋራ ችግሮቻችን ላይ የጋራ መፍትሄ ማስቀመጥ ሲቻል ነው ያሉት ዶክተር እሸቱ በመድረኩም የግጭት መንስኤዎችን ለይቶ በመገምገም ዘላቂ እልባትና መፍትሄ ማበጀት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የሃይማኖት አባቶች የሃይማኖት እሴትን፣ የሃገር ሽማግሌዎች የገጠመንን ፈተና በመቀልበስ፣ ሴቶች ጥበብን፣ ወጣቶች የመሪነት ሚናን በመላበስ የክልሉን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የድርሻቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።
ሚኒስቴሩና የክልሉ ፀጥታ ቢሮ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ከክልሉ የጸጥታ ተቋማት፣ ከሴቶችና ከወጣቶች አደረጃጀቶች፣ ከሃይማኖት አባቶችና ከሃገር ሽማግሌዎች የተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።