የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ትራንስፖርት ውጤታማ የፖሊሲ እርምጃ በአርአያነት የሚወሰድ ነው - የዘርፉ ሙያተኞችና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ትራንስፖርት ውጤታማ የፖሊሲ እርምጃ በአርአያነት የሚወሰድ ነው - የዘርፉ ሙያተኞችና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት
አዲስ አበባ፤ መስከረም 9/2019 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ትራንስፖርት ውጤታማ የፖሊሲ እርምጃ የአፍሪካና የዓለም ሀገራት በአርአያነት ሊወስዱት የሚገባ መሆኑን የዘርፉ ሙያተኞችና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ገለጹ።
የአፍሪካን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ሽግግር ከኖርዲክ ሀገራት የቴክኖሎጂና የኃይል ልማት ልምድ ጋር የሚያገናኘው የኖርዲክ-አፍሪካ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄዱ ይታወቃል።
በጉባኤው የተገኙ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላትና የአለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ትራንስፖርትን ለማስፋፋት የወሰደችው የፖሊሲ እርምጃ እና እያደረገች ያለውን እንቅስቃሴ ለአፍሪካና ለቀሪው ዓለም በአርአያነት የሚጠቀስ መሆኑን ተናግረዋል።
በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የቴክኖሎጂ፣ ኢኖቬሽን፣ ግንኙነትና መሠረተ ልማት ክፍል ዳይሬክተር ሮበርት ታማ ሊሲንጌ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በአህጉራችን በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መስክ ውጤት እያመጡ ያሉ ሀገራት እንደ ኢትዮጵያ ግልጽ ራዕይ፣ ስትራቴጂና የትግበራ እቅድ ያላቸው ናቸው።
ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ከኢትዮጵያ ልምድ በመውሰድ በበቂ መሠረተ ልማትና የሀገር ውስጥ ባለሙያዎች አቅም ግንባታ ላይ ኢንቨስት ማድረግ እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ትራንስፖርት ዘርፍ እያደረገች ያለው ሽግግር ጠንካራ የፖለቲካ ቁርጠኝነትን የሚያሳይና ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የፊንላንድ ኤምባሲ የንግድና ልማት ሃላፊ ቶሚ ሳርኬ፤ የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቴክኖሎጂን በማስፋፋት ውጤታማ ሥራ እሰራች ነው ብለዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ በአረንጓዴ ትራንስፖርት ዘርፍ የታዩት ለውጦች እጅግ ማራኪ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የተወሰዱት የፖሊሲ እርምጃዎችና የመሪዎችን ቁርጠኝነት ህዝቡ ለራዕዩ መሳካት በጋራ እንዲንቀሳቀስ ትልቅ መነሳሳት መፍጠራቸውንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ አረንጓዴ ትራንስፖርትን ለማስፋፋት የምታደርገው ፈጣን ሽግግር የሀገሪቱን ብሩህ የወደፊት አቅጣጫ የሚያመላክት እንደሆነም ተናግረዋል።
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ በስፋት እየገቡ ነው ያሉት ደግሞ የኖርዲክ-አፍሪካ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ጉባኤ የሀሳብ መሪ ሚከል ቤከር አከርቪክ ናቸው።
ይህ ታላቅ ስኬት በአውሮፓና በሌሎች ዓለም ሀገራት በዘርፉ ላይ ለሚሰሩ ባለድርሻ አካላት ትልቅ የአጋርነት ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
በአረንጓዴ ትራንስፖርትም በአረንጓዴ ቴክኖሎጂ ላይ የበለጠ ለመስራት የኢትዮጵያ እንዲሁም የአፍሪካ ጊዜ አሁን በመሆኑ ሁሉም የዚህ አረንጓዴ ሽግግር አካል እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።