ቀጥታ፡

የመስቀል ደመራና ኢሬቻ በዓላት የውጭ ጎብኚዎችን ቀልብ በመሳብ ለሀገር ገጽታ ግንባታ ገንቢ ሚና እየተወጡ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 9/2019 (ኢዜአ):-የመስቀል ደመራና የኢሬቻ የአደባባይ በዓላት የውጭ ጎብኚዎችን ቀልብ በመሳብ ለቱሪዝም ፍሰትና ለሀገር ገጽታ ግንባታ ትልቅ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ።

ኢትዮጵያ ብዝኃ ኃይማኖታዊ፣ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶችን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በሚዳሰሱ እና በማይዳሰሱ ቅርስነት አስመዝግባለች።

በየዓመቱ በመስከረም ወር ከሚከበሩ በዓላት መካከል የመስቀል ደመራ አንዱ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ ሲሆን፣ የኢሬቻ በዓልም በገዳ ሥርዓት ሥር በማይዳሰስ የዓለም ቅርስነት የተመዘገበ የአደባባይ በዓል ነው።

የመስቀል ደመራ በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምዕመናን ዘንድ በታላቅ ኃይማኖታዊ ሥርዓትና ድምቀት በአደባባይ የሚከበር የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎችን ቀልብ የሚስብ በዓል ነው።

ኢሬቻ ደግሞ ከገዳ ሥርዓት የሚቀዳ የኦሮሞ ሕዝብ ታሪካዊና ባህላዊ እሴት ሲሆን፤ የክረምቱ ወቅት አልፎ ብራ ሲጠባ ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት፣ አንድነትና አብሮነት የሚገለጥበት በዓል ነው።

ኢሬቻ በአባ ገዳዎችና በሃደ ሲኒቄዎች መሪነት በባህላዊ አልባሳት ያሸበረቁ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች አማካኝነት በታላቅ ድምቀት የሚከበር የአደባባይ በዓል ነው።

የመስቀል ደመራ፣ የኢሬቻ እና ሌሎች ኃይማኖታዊ፣ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶችም የኢትዮጵያን ውድ ሀብቶችና ገጽታዎች ለዓለም በመግለጥ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎችን ቀልብ እያሳቡ ይገኛሉ።

ይህም የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሀብት በማስተዋወቅና የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በማሳደግ በሀገር ገጽታ ግንባታ ላይ ከፍተኛ ሚና የሚያበረክትበትን ዕድል ፈጥሯል።

በቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም ፕሮሞሽን መሪ ሥራ አስፈጻሚ ተሾመ ተክሉ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ እምቅ የቱሪዝም ሀብቶች አሏት።

የኢትዮጵያ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ የቱሪዝም ሀብቶች፣ በዓላትና ቅርሶችም የቱሪዝም መነቃቃትን በመፍጠር ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በማጎልበት የጎላ አስተዋፅኦ እያበረከቱ መሆኑን ገልጸዋል።

የመስቀል ደመራ፣ ኢሬቻና ሌሎች ኃይማኖታዊና ባህላዊ የአደባባይ በዓላት ሰፊ የቱሪዝም አቅም በመፍጠር ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ባሻገር የኢትዮጵያን እውነተኛ ገጽታ እየገለጡ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።

ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ የሚከበሩት የቡሄ፣ ሻደይ፣ አሸንዳ፣ ጎቤ፣ ሽኖዬ፣ የዘመን መለወጫ፣ የመስቀል ደመራና ኢሬቻ በዓላት ከፍተኛ የጎብኚዎች ቁጥር የሚስተናገዱባቸው ህዝባዊ ሁነቶች ናቸው ብለዋል።

የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላት የኢትዮጵያን እምቅ የቱሪዝም ሀብት ለዓለም በማሳየት፣ የቱሪዝም ኢኮኖሚ መነቃቃት የሚፈጠርባቸውና ማኅበራዊ ትስስር የሚጠናከርባቸው መሆናቸውን ተናግረዋል።

እነዚህ የአደባባይ በዓላት ከኢትዮጵያውያን ባሻገር የውጭ ጎብኚዎች ጭምር በስፋት የሚታደሙባቸው መሆናቸውን አብራርተዋል።

የአደባባይ በዓላቱ በጎብኚዎች ዐይን ተመራጭ መሆናቸው ኢትዮጵያ ያሏትን ድንቅ የቱሪዝም ሀብቶች በማስተዋወቅ የሀገራችንን ገጽታ እንድንገነባ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላት በድምቀት እንዲከበሩ በበዓላቱም በርካታ ጎብኚዎች እንዲታደሙ የሚያስችሉ የዲጂታልና የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም የማስተዋወቅ ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዓላቱ ኃይማኖታዊ እና ባህላዊ እሴታቸውን ጠብቀው በታላቅ ድምቀት እንዲከበሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

የአደባባይ በዓላቱ የቱሪዝም ገቢን ከማሳደግ ባሻገር ለሀገር ገጽታ ግንባታ የሚኖራቸውን ፋይዳ ታሳቢ በማድረግ በታላቅ ድምቀት እንዲከበሩ ከፍተኛ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ባለፉት ዓመታት ቱሪዝም በብዝሃ ኢኮኖሚ ዘርፎች በመካተቱ የተገነቡ የቱሪዝም መዳረሻዎች የውጭ ጎብኚዎችን ትኩረት በመሳብ በዘርፉ የላቀ ውጤት እንዲመዘገብ እያስቻሉ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም