ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከታንዛንያ : ወሳኙ የማጣሪያ ጨዋታ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 9/2019 (ኢዜአ):- ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ኢትዮጵያ ሁለተኛ የምድብ ጨዋታዋን ከታንዛንያ ጋር ዛሬ ታደርጋለች።

ጨዋታው ምሽት ሁለት ሰዓት ላይ በኡሁሩ ስታዲየም ይካሄዳል።

በምድብ አንድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከትናንት በስቲያ ባደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ ከሩዋንዳ ጋር ያለ ግብ አቻ ተለያይቷል።

አዘጋጇ ታንዛንያ በመጀመሪያ ጨዋታዋ ሩዋንዳን 3 ለ 0 ረትታለች።

በአሜሪካው አሰልጣኝ ቤንጃሚን ዚመር የሚመራው ብሔራዊ ቡድን ወደ ግማሽ ፍጻሜው ለማለፍ ታንዛንያን መርታት ይጠበቅበታል።

በአንጻሩ ታንዛንያ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ለመግባት ማሸነፍ ወይም አቻ መውጣት ይበቃታል።

ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ከመስከረም 5 ቀን 2019 ዓ.ም አንስቶ በታንዛንያ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ይገኛል።

በውድድሩ ዘጠኝ ሀገራት በሶስት ምድብ ተከፍለው ጨዋታቸውን በማድረግ ላይ ናቸው።

በምድብ ሁለት ዩጋንዳ፣ ሱዳን እና ጅቡቲ እንዲሁም በምድብ ሶስት ደቡብ ሱዳን፣ ኬንያ እና ብሩንዲ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በጋና እ.አ.አ በ2027 ለሚካሄደው ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በማጣሪያ ውድድሩ የፍጻሜ ተፋላሚ መሆን ይኖርበታል።

ከቀጣናው ሁለት ሀገራት ለአፍሪካ ዋንጫው ያልፋሉ።

የሴካፋ ዞን ማጣሪያ እስከ መስከረም 15 ቀን 2019 ዓ.ም ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም