በአዲስ አበባ በዕውቀትና መልካም ሥነ ምግባር የታነጸ ትውልድ ለማፍራት በሚደረገው ጥረት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ በዕውቀትና መልካም ሥነ ምግባር የታነጸ ትውልድ ለማፍራት በሚደረገው ጥረት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 9/2019 (ኢዜአ):- በአዲስ አበባ የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ በዕውቀትና መልካም ሥነ ምግባር የታነጸ ትውልድ ለማፍራት በሚደረገው ጥረት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ገለጸ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ''ሰላማዊ የመማር ማስተማር፤ ለጋራ አብሮነት'' በሚል መሪ ሀሳብ የ2019 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሂደት የባለድርሻ አካላት ምክክር መድረክ እያካሄደ ይገኛል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ ሳምሶን መለሰ በመድረኩ እንዳሉት፤ የመማር ማስተማር ሂደት ውጤታማነትን ለማላቅ የባለድርሻ ተቋማትና አካላት ቅንጅት ወሳኝ ነው።
ትውልድ የመገንባት ሂደት የአንድ አካል ብቻ ኃላፊነት ባለመሆኑ የ2019 ዓ.ም የመማር ማስተማር ሥራን በስኬት ለማከናወንም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የውይይት መድረኩ ትምህርት ቤቶች ትውልዱ እውቀትን ከመልካም ስብዕና ጋር አጣምሮ የያዘ ብቁ ዜጋ ለማፍራት በሚከናወኑ ተግባራት ከዘርፉ ተዋናዮች ጋር የጋራ መግባባት ለመፍጠር ያግዛል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሌተናል ጀነራል አስራት ደኔሮ በበኩላቸው፤ የትምህርት ተቋማት ሀገርን የሚያጸኑ ዜጎች የሚፈሩባቸው መሆናቸው ገልጸዋል።
በዚህም የትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር አካባቢዎች የሥራ እንቅስቃሴያቸውን ከሚያውኩ ነገሮች መጽዳት አለባቸው ብለዋል።
ትምህርት ቤቶችን ከአዋኪ ነገሮች ለመከላከል የትምህርት አመራሮች፣ ቤተሰብ እና ሌሎች የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ግዴታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስም የዘንድሮ ዓመት የመማር ማስተማር ሂደት ስኬታማ እንዲሆን፣ አዋኪ ድርጊቶችን የመከላከል ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በአዲስ አበባ የአዲሱ የ2019 ዓ.ም በጀት ዓመት የትምህርት ዘመን መስከረም 5 ቀን 2019 ዓ.ም መጀመሩ ይታወሳል።