ቼልሲ በብሬንትፎርድ ተሸነፈ - ኢዜአ አማርኛ
ቼልሲ በብሬንትፎርድ ተሸነፈ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 8/2019 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የአምስተኛ ሳምንት የመጀመሪያ መርሐ ግብር ብሬንትፎርድ ቼልሲን 3 ለ 0 አሸንፏል።
በጂቴክ ኮሙኒቲ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ጄይደን አንቶኒ በ61ኛው ደቂቃ የመጀመሪያውን ጎል አስቆጥሯል።
የቼልሲ ከማዕዘን የተሻገረ ኳስን የመከላከል ድክመት ለግቧ መቆጠር ምክንያት ሆኗል።
ኢጎር ቲያጎ በ81ኛው ሁለተኛውን ጎል ሲያስቆጥር ፋቢዮ ካርቫሊዮ በ94ኛው ደቂቃ ሶስተኛውን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ቼልሲ በጨዋታው ደካማ እንቅስቃሴ ያደረገ ሲሆን የግብ እድሎችን መፍጠር ተስኖታል።
የምዕራብ ለንደን ደርቢ በብሬንትፎርድ አሸናፊነት ተጠናቋል።
በውድድር ዓመቱ ሁለተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ቼልሲ በስድስት ነጥብ ከነበረበት ስድስተኛ ደረጃ ወደ ሰባተኛ ዝቅ ብሏል። ቡድኑ ባለፉት ሶስት የሊግ ጨዋታዎች ከድል ርቋል።
በሊጉ ሁለተኛ ድሉን ያስመዘገበው ብሬንትፎርድ በዘጠኝ ነጥብ ከሰባተኛ ደረጃ ወደ ሶስተኛ ከፍ ያለ ሲሆን እስከ አሁን በውድድር ዓመቱ ሽንፈት አላስተናገደም።
የሊጉ አምስተኛ ሳምንት መርሐ ግብር እስከ መስከረም 10 ቀን 2019 ዓ.ም ይቆያል።