የአደባባይ በዓላት የቱሪዝም ዘርፉን በማነቃቃት ረገድ ያላቸው አበርክቶ የጎላ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአደባባይ በዓላት የቱሪዝም ዘርፉን በማነቃቃት ረገድ ያላቸው አበርክቶ የጎላ ነው
ሆሳዕና ፤ መስከረም 9/2019(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሚከበሩ የአደባባይ በዓላት የቱሪዝም ዘርፉን በማነቃቃት ረገድ ያላቸው አበርክቶ የጎላ መሆኑን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገለፀ።
የአደባባይ በዓላት የአንድን ማህበረሰብ ባህላዊ እሴትና ታሪክ በግልፅ የሚያሳዩ ከመሆናቸው ባሻገር፣ ለአገር ውስጥና ለውጭ ሀገር ጎብኚዎች ሳቢ የመስህብ ሀብት በመሆን ለቱሪዝም ዘርፉ ማደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታሉ።
በዓላቱ በሚከበሩበት ወቅት በርካታ ተጓዦች ወደ አከባቢዎቹ የሚመጡ በመሆናቸው፣ አዳዲስ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በስፋት ለማስተዋወቅና የጎብኚዎችን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ ለማሳደግ ትልቅ እድልን ይፈጥራሉ።
በተጨማሪም የነዚህ በዓላት መከበር በቱሪዝም ዘርፉ አካባቢ የሚከናወነውን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ ያነቃቃዋል።
ጎብኚዎች በብዛት ወደ ክልሎች በሚገቡበት ወቅት በሆቴሎች፣ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ በትራንስፖርት፣ በባህላዊ አልባሳትና ጌጣጌጥ ሽያጭ ላይ የሚፈጠረው የገበያ ፍላጎት ይጨምራል።
ይህንን አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል መንገሻ፤ በክልሉ የሚከበሩ የአደባባይ በዓላት የቱሪዝም ዘርፉን በማነቃቃት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ክልሉ በቱሪዝም ዘርፍ ያለውን ፀጋ በመለየት ከዘርፉ የሚገኝን ገቢ ለማሳደግ የሚያስችል ዘርፈ ብዙ አማራጭ እየተተገበረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዚህም ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ የቱሪዝም መዳረሻዎች ተለይተው የማልማት፣ የማስተዋወቅ ስራ እየተሰራ በመሆኑ የጎብኚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ስለመምጣቱም ጠቁመዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ጎብኚዎችን በማስተናገድ ከ 2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ከቱሪዝም ዘርፉ ለማመንጨት ግብ ተጥሎ ወደ ትግበራ ምዕራፍ ተገብቷል ነው ያሉት።
በአብዛኛው በክልሉ ህዝቦች በዘመን መለወጫነት የሚከበሩ በሀድያ ያሆዴ፣ በከምባታ መሳላ፣ በየም ሄቦ እና በጉራጌ መስቀል እና ሌሎችም በመስከረም ወር በደማቅ ስነ-ስርዓት የሚከበሩ የአደባባይ በዓላት ስለመሆናቸው አንስተዋል።
እነዚህን ባህላዊ የመስህብ ሀብቶችን የማስጠበቅ፣ የማልማት፣ የማስተዋወቅና ለቱሪዝም ዘርፉ የገቢ ምንጭ የማድረግ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
የዘመን መለወጫ በዓላቱን ለማክበር የአካባቢው ተወላጆችና በበዓሉ የሚታደሙ ጎብኚዎች ወደ ክልሉ በስፋት ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።
ይህም የሆቴሎች፣ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትና የባህላዊ አልባሳት ሽያጭና ከሌሎች መስኮች የሚገኘው ገቢ የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንደሚያሳድገውም አስረድተዋል።
የሲና አስጎብኚ ድርጅት ባለቤት ለምለምወርቅ ሀይለማርያም በበኩሏ በክልሉ የሚከበሩ ህዝባዊና ሀይማኖታዊ በዓላት ለቱሪዝም ዘርፉ ከፍተኛ መነቃቃትን እንደሚፈጥሩ ገልጻለች።
የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ጎብኚዎች በክልሉ የሚገኙ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ የቱሪዝም መዳረሻዎችን የመጎብኘት ፍላጎት እያደገ ስለመምጣቱ ጠቅሳ፤ የተለያዩ የመስህብ ስፍራዎችን በማስጎብኘት ከዘርፉ ተጠቃሚ እየሆነች ስለመሆኑም አስረድታለች።