የሊጉ መሪ አርሰናል ከብራይተን ጋር ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
የሊጉ መሪ አርሰናል ከብራይተን ጋር ይጫወታል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 9/2019 (ኢዜአ):- በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ አምስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ከቀኑ 11 ሰዓት ብራይተን ከአርሰናል በአሜክስ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
ብራይተን በሰባት ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
የወቅቱ የሊጉ ሻምፒዮን አርሰናል በ12 ነጥብ የሊጉ አናት ላይ ተቀምጧል።
በአራተኛ ሳምንት መርሐ ግብር ብራይተን ከሜዳው ውጪ አዲስ አዳጊውን ኮቨንተሪ ሲቲን 5 ለ 0 መርታቱ የሚታወስ ነው።
አርሰናል በሊጉ ያደረጋቸውን አራት ጨዋታዎች በማሸነፍ ጠንካራ ጅማሮ አድርጓል።
መድፈኞቹ ካሸነፉ ከተከታያቸው ማንችስተር ሲቲ ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሶስት ከፍ ያደርጋሉ።
ባለሜዳው ብራይተን ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ወደ ሜዳ ይገባል።
ጨዋታው ተመጣጣኝ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።
በሌላኛው መርሐ ግብር ቶተንሃም ሆትስፐርስ ከአስቶንቪላ ይጫወታሉ።
ቶተንሃም ሆትስፐርስ በሁለት ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዟል። አንድ ነጥብ ያለው አስቶንቪላ በበኩሉ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።
ባለሜዳው ቶተንሃም እስከ አሁን በሊጉ ምንም ጎል ማስቆጠር አልቻለም። አስቶንቪላም በአራት ጨዋታዎች ከመረብ ጋር ማገናኘት የቻለው አንድ ግብ ብቻ ነው።
በሊጉ በጣም ደካማ አጀማመር ያሳዩት ሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ ሶስት ነጥባቸውን ለማግኘት ይፋለማሉ።
ኤቨርተን ከኤፕስዊች ታውን እና ኒውካስትል ዩናይትድ ከሁል ሲቲ በተመሳሳይ ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ምሽት 1 ሰዓት ከ30 ላይ ኖቲንግሃም ፎረስት ከኮቨንተሪ ሲቲ በሲቲ ግራንውንድ ስታዲየም ይጫወታሉ።