ቀጥታ፡

በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ሊደርስ የሚችልን ተፅዕኖ ምላሽ መስጠት የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 9/2019 (ኢዜአ):- በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ሊደርስ የሚችልን ተፅዕኖ ምላሽ መስጠት የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

የዓለም የሚቲዮሮሎጂ ድርጅት የኤልኒኖ ክስተት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የሙቀት መጨመርና የአየር ንብረት መዛባት እንደሚያስከትል አስታውቋል።

ይህ ክስተት በምሥራቅ አፍሪካና በኢትዮጵያ በአንዳንድ አካባቢዎች ከፍተኛ ድርቅ፣ በሌሎችም ከፍተኛ ጎርፍ ሊያስከትል እንደሚችል መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አይድሩስ ሐሰን ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ኤልኒኖ ቀደም ሲል በየአሥር እና አምስት ዓመቱ ተደጋጋሚ ክስተቶች አሳይቷል።

ቀደም ሲል በምሥራቅ አፍሪካ ከተከሰተው የኤልኒኖ አደጋ በርካታ ትምህርቶች መወሰዳቸውን ገልጸዋል።

የዓለም አቀፍ እና የኢትዮጵያ ሚቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በ2018/19 ዓ.ም. አዲስ የኤልኒኖ ክስተት እንደሚከሰት ይጠበቃል።

በመሆኑም ኮሚሽኑ ይህንን ተጽዕኖ መቀነስ የሚያስችሉ አጠቃላይ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በስፋት እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ተቋሙ ወቅታዊ ችግሮችን ብቻ ሳይሆን፣ ዘላቂ ችግሮችን ጭምር የሚፈቱበትን አቅም በመገንባት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ለኤልኒኖ ክስተት ያለውን ተጋላጭነት መጠን የመለየት፣ የመቀነሻ እና የማቋቋሚያ ስትራቴጂ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል።

በዝናብ እጥረት ሳቢያ የሚከሰቱ ጉዳቶችን አስቀድሞ ለመከላከል በኮሚሽኑ አስተባባሪነት ከፌዴራል እስከ ታችኛው መዋቅር ካሉ ሴክተሮች ጋር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በደቡብ ምሥራቅ እና ደቡብ ኢትዮጵያ በኤልኒኖ ምክንያት ሊከሰት ከሚችለው የጎርፍ አደጋ ጋር ተያይዞ በፌዴራል እና በክልል ደረጃ አስፈላጊ የምግብ፣ የምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች እና ቅጽበታዊ መሣሪያዎች ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

ይህ አስቀድሞ የመከላከል እና የማስተባበር ሥራ ለአደጋው ተጋላጭ የሆኑ ዜጎችን ደህንነት በመጠበቅ ሊደርስ የሚችለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሰዋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ሰው ሠራሽም ይሁን የተፈጥሮ አደጋዎችን በራስ አቅም ለመቋቋም የሚያስችል ጠንካራ አቅምም እየተገነባ መሆኑን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ከለውጡ ወዲህ ከፍተኛ የስትራቴጂክ ለውጥ በማድረግ አዲስ ፖሊሲና አዋጅ ሥራ ላይ ማዋሉን አስታውቀዋል።

በሕግ ማዕቀፎቹ መሰረት ሰው ሠራሽም ሆነ የተፈጥሮ አደጋዎችን ከውጭ እርዳታ ጥገኝነት ነፃ በሆነ መልኩ በራስ አቅም ለመቋቋም የሚያስችል ጠንካራ አቅም እየተገነባ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ሰብአዊ ድጋፍን በራስ አቅም ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ ለሌሎች አገራት ጭምር እገዛ የሚያደርግ ‘ኢትዮጵያን ኤድ’ የተሰኘ ተቋም ለመመስረት ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።

የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቱን ለማጠናከርና ለማዘመን ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ብሔራዊ የአስቸካይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከል መደራጀቱንም ገልጸዋል።

እነዚህ የተደረጉ ተቋማዊ ዝግጅቶችና አዳዲስ አሠራሮች አገሪቱ ለአደጋ የምታደርገውን ምላሽ ሰጪነት በዘላቂነት እንደሚያጠናክር አብራርተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም