በዓለም አትሌቲክስ የጎዳና ላይ ሩጫ ሻምፒዮና ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉባቸው የፍጻሜ ውድድሮች ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
በዓለም አትሌቲክስ የጎዳና ላይ ሩጫ ሻምፒዮና ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉባቸው የፍጻሜ ውድድሮች ይካሄዳሉ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 9/2019 (ኢዜአ):- ሁለተኛው የዓለም አትሌቲክስ የጎዳና ላይ ሩጫ ሻምፒዮና ነገና ከነገ በስቲያ በዴንማርክ ኮፐንሃገን ይካሄዳል።
በሻምፒዮናው ላይ ከ86 ሀገራት የተወጣጡ 496 አትሌቶች ይሳተፋሉ።
የዓለም አትሌቲክስ የስደተኞች አትሌቲክስ ቡድንም በዚህ ውድድር ላይ ተካፋይ ነው።
በተጨማሪም ከአትሌቶቹ ውጪ ከ65 ሺህ በላይ ሰዎች ተሳትፎ ያደርጋሉ።
ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው ላይ ከሚሳተፉ ሀገራት መካከል አንዷ ናት። በሁለቱም ጾታዎች ተጠባባቂዎችን ጨምሮ 18 አትሌቶችን ታሳትፋለች።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑካን ቡድን ለሻምፒዮናው በአዲስ አበባ ዝግጅቱን አድርጓል።
አትሌቶቹም ከኮፐንሀገን የአየር ንብረትና የውድድር ሁኔታ ጋር በተሻለ ሁኔታ ለመላመድ እንጦጦ፣ በጣፎ፣ ቃሊቲ፣ ሰበታ እና ሰንዳፋን ጨምሮ በተለያዩ ስፍራዎች ልምምዳቸውን አከናውነዋል።
ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው ላይ በወንዶችና በሴቶች ግማሽ ማራቶን፣ በወንዶችና በሴቶች አምስት ኪሎ ሜትር እንዲሁም በሴቶች አንድ ማይል ውድድሮች ላይ ተሳትፎ ታደርጋለች።
ዛሬ በሻምፒዮናው መክፈቻ ቀን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳፉባቸው ውድድሮች ይካሄዳሉ።
ከቀኑ 5 ሰዓት ከ10 በሚደረገው የአንድ ማይል የሴቶች ውድድር ፍሬወይኒ ኃይሉ እና ብርቄ ኃየሎም ይሳተፋሉ።
ልቅና አምባው እና አለሽኝ ባወቀ ከቀኑ 9 ሰዓት ከ10 በሚካሄደው የአምስት ኪሎ ሜትር ውድድር ላይ የሚሳተፉ አትሌቶች ናቸው።
ከቀኑ 9 ሰዓት ከ40 ላይ በሚደረገው የአምስት ኪሎ ሜትር ፍጻሜ መዝገቡ ስሜ እና አዲሱ ይሁኔ ይሳተፋሉ።
የዓለም አትሌቲክስ የጎዳና ላይ ሩጫ ሻምፒዮና የቀድሞውን የዓለም አትሌቲክስ የግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና የተካ ውድድር ነው።
የግማሽ ማራቶን ሻምፒዮናው ከእ.አ.አ 1992 እስከ 2020 ሲካሄድ ቆይቷል።
እ.አ.አ በ2023 ስያሜውን ቀይሮ የዓለም አትሌቲክስ የጎዳና ላይ ሩጫ ሻምፒዮና የተባለ ሲሆን የመጀመሪያው ውድድር በዛው ዓመት በላቲቪያ ሪጋ ተካሄዷል።
የአሁኑ ሻምፒዮና ከዚህ ቀደም ከነበረው የግማሽ ማራቶን በተጨማሪ የአምስት ኪሎ ሜትር እና የአንድ ማይል ውድድሮች ተካተውበታል።
ኢትዮጵያ ከእ.አ.አ 1992 እስከ 2023 ባለው ጊዜ ውስጥ በዓለም አትሌቲክስ የግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና፣ ስያሜውን ቀይሮ በላቲቪያ ሪጋ የተካሄደውን የዓለም አትሌቲክስ የጎዳና ላይ ሩጫ ሻምፒዮናን ጨምሮ በግል እና በቡድን ያገኘቻቸው አጠቃላይ ሜዳሊያዎች ብዛት 57 ናቸው።
ኢትዮጵያ 15 የወርቅ፣ 22 የብር እና 20 የነሐስ በድምሩ 57 ሜዳሊያዎችን አግኝታለች።
እ.አ.አ በ2023 በላቲቪያ ሪጋ በተካሄደው የመጀመሪያው የዓለም የጎዳና ላይ ሩጫ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ 2 ወርቅ፣ 4 ብር እና 1 ነሐስ በጠቅላላው ሰባት ሜዳሊያዎች በማግኘት ኬንያን ተከትላ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው።