ቀጥታ፡

ኮሞሮስ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ለማጠናከር ጽኑ ፍላጎት አላት

አዲስ አበባ፤ መስከረም 9/2019 (ኢዜአ):- ኮሞሮስ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር የጋራ ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ መልኩ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን አምባሳደር ዩሱፍ ሞንዶሃ አሱማኒ ገለጹ።

የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መምጣቱን በኢትዮጵያ የኮሞሮስ አምባሳደር እና የአፍሪካ ህብረት ቋሚ መልዕክተኛ ዩሱፍ ሞንዶሃ አሱማኒ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።

ሁለቱ ሀገራት የጋራ ኮሚሽን ለመመስረት የሚያስችል ስምምነትን ለመፈራረም የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መድረሳቸውን ጠቅሰው፤ ኮሚሽኑ ትብብሩን የበለጠ ለማጎልበት እንደሚያስችልም አመልክተዋል።

የኢኮኖሚ ትብብርን ማጠናከር የሁለቱ ሀገራት የቅድሚያ ትኩረት እንደሆነም ነው ያነሱት።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሁለቱ ሀገራት የንግድ ልውውጥ መስፋት እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ትብብር መጠናከር እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።

አየር መንገዱ ወደ ኮሞሮስ መብረር የጀመረበትን የ10ኛ ዓመትን በጋር ለማክበርም ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሲቪል አቪዬሽን ዘርፍ ለአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች እየተሰጠ ያለው የረጅም ጊዜ ስልጠና የኮሞሮስን ብሔራዊ አቅም በማሳደግ ላይ እንደሚገኝ ነው ያመለከቱት።

የኮሞሮስ የንግድ ማህበረሰብ ከኢትዮጵያ አቻ ተቋማት ጋር ያላቸውን የንግድ ትስስር በየሀገራቱ የንግድ ምክር ቤቶች በኩል ይበልጥ ለማጠናከር የሚችሉባቸው እድሎች እንዳሉም ነው አምባሳደሩ ያነሱት።

የፀጥታ ትብብሩን ለማጠናከር የኮሞሮስ ፖሊስ ተቋም ከፍተኛ አመራሮችን ያቀፈ ልዑክ ኢትዮጵያን መጎብኘቱን ያስታወሱት አምባሳደሩ፤ ልዑኩ በተደራጀ ወንጀል እና በአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር መከላከል ዙሪያ የኢትዮጵያን ልምድ መቅሰሙን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ የኢነርጂ ልማት ለአፍሪካ ልማት እና ለቀጣናው የኤሌክትሪክ አቅርቦት ተደራሽነት ወሳኝ ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያን ሀገራዊ የምክክር ሂደት ያደነቁት አምባሳደሩ ሰላምና መረጋጋት ለአፍሪካ ልማት ጉልህ አበርክቶ እንዳለውም ገልጸዋል።

ኮሞሮስ የምታስተናግደውን የህንድ ውቅያኖስ ደሴቶች ጨዋታዎችን ጨምሮ በቱሪዝም፣ በአገልግሎት ዘርፍ እና በስፖርት ሁነቶች ዝግጅት ከኢትዮጵያ ልምድ የመቅሰም ፍላጎት እንዳላት ነው የገለጹት።

በአጠቃላይ ኮሞሮስ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር የጋራ ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ መልኩ ለማጠናከር ጽኑ ፍላጎት እንዳላት አምባሳደሩ ተናግረዋል።

ኮሞሮስ በአዲስ አበባ ኤምባሲዋን ከከፈተችበት ከእ.ኤ.አ 2011 አንስቶ እያደገ የመጣው ግንኙነት አሁን ላይ ትብብሩን በተለያዩ ዘርፎች ይበልጥ ለማጠናከር ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም