የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ ፤ መስከረም 8/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን የክልሉን የቱሪዝም መስህቦች በጋራ ለማስተዋወቅ የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።
ስምምነቱን የኢዜአ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ፍፁም እሸት ሽመልስ እና የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ዱጋ ተፈራርመውታል።
የኢዜአ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ፍፁም እሸት ሽመልስ በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት እንደገለጹት፤ የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ከሀገራዊ ለውጡ ማግስት ጀምሮ ለዘርፉ የተሰጠውን ልዩ ትኩረትና ቦታ በመረዳት ወደ ሥራ የገባ ተቋም ነው።
ኢትዮጵያ ያላትን በርካታ የቱሪዝም ሀብቶች ለዓለም ማስተዋወቅ አስፈላጊ መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ ለአፍሪካና ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በርካታ የዴሞክራሲና የአስተዳደር ትምህርቶችን ሊሰጥ የሚችለውን የገዳ ስርዓት ለአብነት መጥቀስ እንደሚቻል አብራርተዋል።
የኢዜአ ዋና ተልዕኮዎች ሀገራዊ መግባባትን መፍጠር እና የሀገርን በጎ ገጽታ በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስተዋወቅ መሆናቸውን ገልጸው፤ ይህንም በ"ፐልስ ኦፍ አፍሪካ" (Pulse of Africa) ሚዲያ ለአፍሪካውያንና ለዓለም ማህበረሰብ እንደሚያስተዋውቁ ተናግረዋል።
ይህ ስምምነትም እነዚህን ተልዕኮዎች በተግባር ለመወጣት ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን የሚያከናውናቸውን ሀገር ተሻጋሪ ሥራዎች በእንግሊዝኛ፣ በአረብኛ እና በሌሎች ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ለዓለም ለማስተዋወቅ በጋራ እንደሚሰሩም አስታውቀዋል።
የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ዱጋ በበኩላቸው፤ አንጋፋውና ሰፊ ተደራሽነት ያለው ኢዜአ ከኮሚሽኑ ጋር መስራቱ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ገልፀዋል።
የቱሪዝም ዘርፉ ያለ ፕሮሞሽን እና የመረጃ ተደራሽነት ሊያድግ እንደማይችል ገልጸው፣ ከኢዜአ እና ከፐልስ ኦፍ አፍሪካ ጋር የተደረገው አጋርነት የስራውን ውጤታማነት ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው ተናግረዋል።
ሁለቱ ተቋማት የቱሪዝም አጀንዳዎችን በጋራ እንደሚያስፈጽሙና ቱሪዝምን የአፍሪካ ህዝቦችን ማስተሳሰሪያ መንገድ አድርገው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
የኢሬቻ በዓልን ምክንያት በማድረግ በኦሮሚያ ቱሪዝም ሳምንት ላይ ለመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ራሱን የቻለ የኤግዚቢሽን ቦታ እንደሚሰጥ ጠቁመው፤ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገራት ከሚመጡ ጎብኚዎች ጋር ትስስር እንዲፈጠር ዝግጅት መደረጉንም አስታውቀዋል።