ቀጥታ፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የስራ እድል ፈጠራ አማራጮችን ወደ ውጤት የመቀየር ተግባራት ይጠናከራሉ

ሆሳዕና ፤ መስከረም 8/2019 (ኢዜአ) ፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የስራ እድል ፈጠራ አማራጮችን  ወደ ውጤት የመቀየር ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡ 

የክልሉ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ያለፈውን በጀት ዓመት አፈጻጸም እና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ የሚመክር መድረክ በሆሳዕና ከተማ አካሄዷል።


 

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ልዩ አማካሪ ንጉሤ አስረስ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በክልሉ የሥራ ዕድል ፈጠራ አማራጮችን ወደ ውጤት በመቀየር የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ተግባራት ይጠናከራሉ።

በተለይም በዘርፉ የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የአሠራር እና የድጋፍ ማዕቀፎች መዘርጋታቸውን ጠቁመዋል።

የሥራ ዕድል ፈጠራውን ለማበረታታትም ኢንተርፕራይዞችን በመደገፍ የተግባር ሥልጠና እንዲሰጡ መደረጉን ጠቅሰዋል።

በዘርፉ የተመዘገቡ ስኬቶችን ለማጠናከር የባለድርሻ አካላት ርብርብ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።


 

የክልሉ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ በበኩላቸው፤ በክልሉ በበጀት ዓመቱ የሥራ ዕድል ፈጠራን በማስፋፋት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።

በዚህም በግብርና፣ በአገልግሎት እና በኢንዱስትሪው ዘርፍ ከ450 ሺህ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ ከ5 ሺህ 900 ሄክታር በላይ መሬት እና 600 የሚጠጉ ሼዶች ለኢንተርፕራይዞች ተዘጋጅተዋል ብለዋል።

ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ የብድር አቅርቦት መዘጋጀቱን እና ቀደም ባሉት ዓመታት ሼዶች ወስደው ሀብት ያፈሩ አንቀሳቃሾችን ለማሸጋገር ግብ ተይዞ ወደ ትግበራ ምዕራፍ መገባቱንም ኃላፊው ገልጸዋል።

የስልጤ ዞን የሥራ ዕድል ፈጠራ እና ኢንተርፕራይዞች ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ አብዱራህማን ወርቅቾ፣ ዞኑ በሥራ ዕድል ፈጠራ ያሉ ጸጋዎችን ለይቶ በመጠቀም ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም ወጣቶችን በሥራ ዕድል ፈጠራው ተጠቃሚ ለማድረግ ከ1 ሺህ 350 ሄክታር በላይ መሬት እና ከ150 በላይ አዳዲስ ሼዶችን ገንብቶ ለማስረከብ ታቅዷል ብለዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የክልል፣ የዞን፣ የልዩ ወረዳ፣ የወረዳ እና የከተማ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም