ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ በሚኖራት ሚና ላይ ያለው ዓለም አቀፍ መግባባት እያደገ መጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ በሚኖራት ሚና ላይ ያለው ዓለም አቀፍ መግባባት እያደገ መጥቷል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 8/2019 (ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ ባላት ሚና ዓለም አቀፋዊ መግባባት እየተፈጠረበትና አጀንዳው ተቀባይነቱ እያደገ መምጣቱን የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተመራማሪ ግዛቸው አስራት (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ፍላጎት ለቀይ ባህር ቀጣና ትልቅ እድል መሆኑንም ከፍተኛ ተመራማሪው ለኢዜአ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ፍትሃዊ እና ተቀባይነት ያለው ስትራቴጂካዊ መብት መሆኑንም ገልጸዋል ።
የሀገሪቱ የህዝብ ቁጥር ማደግ፣ የኢኮኖሚው እየሰፋ መሄድ፣ የንግድ ልውውጥ ማደግ እንዲሁም ሀገራዊ እና ቀጣናዊ የጸጥታ ዋስትናን በአስተማማኝ ሁኔታ ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆን ለዚህ ጥያቄ ዋና ዋና ምክንያቶች እንደሆኑ ነው ያብራሩት።
ሀገሪቱ ከቀይ ባህር ጋር ያላት ጂኦግራፊያዊ ቅርበት እና ከቀጣናው ወደቦች ጋር የነበራት ታሪካዊ ትስስር ዘላቂ የባህር መውጫ ለማግኘት ለምታነሳቸው ጥያቄዎች ጠንካራ መሰረት እንደሆነም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ በባህሩ አቅራቢያ መገኘት እና በኢኮኖሚውም ሆነ በጸጥታው መስክ ትልቅ ሚና መጫወት እንዳለባት የጋራ ግንዛቤ እንዳለም ነው የገለጹት ከፍተኛ ተመራማሪው።
ለዚህ ስኬትም ጎረቤት ሀገራት እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በጋራ መተማመንና በትብብር መስራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ እውነተኛ ዓላማ በግልጽ መረዳት እንደሚገባ ተመራማሪው አንስተዋል።
የጂኦ-ፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ጉዳዮች ከየብስ እስከ ባህር የተሳሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ቀጣናዊ የፀጥታ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትም የየብስና የባህር ደህንነትን ነጣጥሎ ከማየት ይልቅ፣ በጋራ ስጋቶችና ጥቅሞች ላይ ያተኮረ ትብብር መፍጠር እንደሚገባ አመልክተዋል።
በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ ወደ ባህር በር መመለስ ለቀጣናው ሰላም፣ ለቀጣናዊ ትስስር እና ለምስራቅ አፍሪካ የጋራ ደህንነት ወሳኝ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያን በቀይ ባህር መድረክ ላይ መሳተፍ ለቀጣናው ትልቅ እድል ነው ሲሉም አክለዋል።
ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ እና የፀጥታ ስርዓት ጋር ያላት ቁርኝት ጥልቅ በመሆኑ፣ በቀይ ባህር እና የባህር መስመሮችን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ በባለቤትነት መሳተፍ እንዳለባት አሳስበዋል።
ሰፊ የህዝብ ቁጥር ያላት፣ በማደግ ላይ ያለ ኢኮኖሚ እና ስትራቴጂካዊ ቦታ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘቷ በምስራቅ አፍሪካ እና በቀይ ባህር የባህር ፀጥታን ለማስጠበቅ የግድ ሊሟላ የሚገባው መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን ከፍተኛ ተመራማሪው አስገንዝበዋል።