የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ፈጣሪነት አስቀድሞ የተረዳው - ብሪክስ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ፈጣሪነት አስቀድሞ የተረዳው - ብሪክስ
በመቅደስ ወልዴ
ብሪክስ እ.ኤ.አ በ2009 ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ተፅዕኖ ፈጣሪነታቸው በፍጥነት እያደጉ ባሉት በቻይና፣ ሩሲያ፣ ህንድ እና ብራዚል የተመሰረተ የደቡብ ደቡብ ትብብር ነው። ብሪክ /BRIC/ በሚል መጠሪያ የመጀመሪየውን ስብሰባውን ያደረገውም በወርሃ ሰኔ እ.ኤ.አ በ2009 በሩሲያዋ የካተሪንበርግ ከተማ ነበር። ጥምረቱ እ.ኤ.አ 2011 ደቡብ አፍሪካን በማካተት ስያሜውን ወደ ብሪክስ /BRICS/ ቀይሯል።
የማህበራዊና የባህል መስተጋብር፣ የጂኦ ፖለቲካና የባለብዙ ወገን ትስስር፣ የኢኮኖሚና የፋይናንስ ትብብር በመፍጠር የጸጥታ፣ የህዝብ ለህዝብና ማህበራዊ ጉዳዮችን ዕድገት ማሳለጥ ያለመ ነው። ኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ የተባበሩት ዐረብ ኢምሬቶች፣ ሳዑዲ ዓረቢያና ኢራን እ.ኤ.አ በ2024 ቀጥሎም ኢንዶኔዥያ እ.ኤ.አ በ2025 ጥምረቱን መቀላቀላቸውን ከብሪክስ ድረገጽ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
እንደ መረጃው ከሆነ ጥምረቱ የዓለምን 49 ነጥብ 5 በመቶ የህዝብ ብዛት የሚሸፍኑ 11 ሀገራትን በአባልነት የያዘ እንዲሁም የዓለማችንን 40 በመቶ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት የሚሸፍን ስብስብ ነው። ብሪክስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፅዕኖ ፈጣሪነትን ማሳደግ፣ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ እንዲሁም እንደ መንግስታቱ ድርጅትና መሰል ዓለም አቀፍ ተቋማት የዘረጉት ኢ-ፍትሐዊ ተቋማዊ አሰራር እንዲሻሻል ተፅዕኖ በመፍጠር ተጨባጭ ለውጥ የማየት ግብ ይዟል።
ኢትዮጵያ እንዴት የብሪክስ አባል ሆነች
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጠንካራ እና በሳል ዲፕሎማሲያዊ ጥረት የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ተሰሚነት አቅምና ተፅዕኖ ፈጣሪነት እያደገ መጥቷል። በዚህም ኢትዮጵያ የአፍሪካ መግቢያ በር፣ የአፍሪካ ህብረት መስራችና መቀመጫ፣ የተለያዩ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት መገኛ፤ የዲፕሎማቶች መናኸሪያ፣ ሰፊ ህዝብና በፍጥነት እያደገ ያለ ኢኮኖሚ ያላት የአፍሪካውያን የአይን ማረፊያ ሆናለች።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን መቀነስና መቋቋም በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በኮሪደር ልማት፣ በወንዝ ዳርቻዎች እንዲሁም በገጠርና በከተሞች ያስመዘገበቻቸው የልማት ውጤቶች የዓለም ቀልብ ስቧል። በአህጉርና በዓለም አቀፍ መድረኮች የራሷን ብሔራዊ ጥቅም ከማስከበር ባለፈ አፍሪካውያንን በመወከል ድምጽ በማስማት ተፅዕኖ ፈጣሪነቷን አሳይታለች።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላት ተጽዕኖ ፈጣሪነት፣ ለጋራ ልማት ለትብብርና ለፍትሐዊ ተጠቃሚነት የምታደርገው ጥረትና ባላት የጠራ የዲፕሎማሲና የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የብሪክስ ጥምረትን እንድትቀላቀል በር ከፍቶላታል። በዚህም የኢትዮጵያ የብሪክስ ጥምረት አባልነት ተቀባይነት አግኝቶ እ.ኤ.አ በወርሃ ጥር 2024 በይፋ ተቀላቅላለች።
ኢትዮጵያ ጥምረቱን እንድትቀላቀል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን መድረኮች ብስለት የተሞላበት የዲፕሎማሲ ጥረት ስለማድረጋቸው በወቅቱ በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት አምባሳደር ሙክታር ከድር (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ መግለጻቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የጥምረቱ አባል መሆን የሚያስችሏትን አሳማኝ ምክንያቶች ሲያስረዱም ኢትዮጵያ ነጻነቷን ያስጠበቀች፣ ለተገፉ ሀገራት ድምፅ የሆነች፣ ለአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት መመስረት ሰፊ ሚና የተጫወተች ሀገር መሆኗን እና ሁለንተናዊ የለውጥ ጉዞ ላይ የምትገኝ ሀገር መሆኗን በማንሳት የደቡብ - ደቡብ ትብብርን ለማጠናከር ይህችን ታላቅ ሀገር ማካተት ተገቢ ነው ሲሉ በአፅንኦት ማስረዳታቸውና ማሳመናቸው ጥያቄው ተቀባይነት እንዲያገኝ አስችሏል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዲፕሎማሲ አሰራር ብስለትን ካረጋገጡ ሂደቶች መካከል ኢትዮጵያን የብሪክስ ጥምረት አባል ለማድረግ የተጠቀሙት የዲፕሎማሲ ስልት ተጠቃሽ ነው። ይህውም ኢትዮጵያን የጥምረቱ አባል ማድረግ ለጥምረቱ አባል ሀገራት እና በጥቅሉ ለጥምረቱ የሚያስገኘውን ጠቀሜታ በተመለከተ ለአባል ሀገራት መሪዎች በተናጥልና በጋራ መድረኮች ተገቢውን ግንዛቤ ማስጨበጣቸው ዋነኛው ነው።
በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የጥምረቱ አባል እንድትሆን ያቀረቧቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ስትራቴጂካዊ አመክንዮዎች የጥምረቱን አባል ሀገራት ልብ መግዛቱ ጥያቄው አወንታዊ ምላሽ እንዲያገኝ አስችሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በወቅቱ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ በባለ ብዙ ወገን ዲፕለማሲ መስክ ያላትን ተደማጭነት የሚያሳይ መሆኑንና በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በግብርና እንዲሁም በሀገር ውስጥ ጥቅል ምርት እድገት እያስመዘገበችው ያለው ስኬት የአባልነት ጥያቄዋ ተቀባይነት እንዲያገኝ ከፍተኛ ሚና ማበርከታቸውን ማብራራታቸው የሚታወስ ነው፡፡
ብሪክስ ለኢትዮጵያ ምኗ ነው
የኢትዮጵያ የጥምረቱ አባል መሆን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ስትራቴጂካዊ ጥቅሞችን ታሳቢ ያደረገ ነው። ብሪክስ በጠንካራና የተቀናጀ ዲፕሎማሲ የጋራ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አቅም በመፍጠር አብሮ ማደግን መዳረሻው አድርጓል። የኢትዮጵያ የብሪክስ ጥምረት አባልነትም የዚህ ጥቅም ተጋሪነትን መርህ ታሳቢ ያደረገ ነው።
ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል በመሆኗ በፋይናንስና የኢንቨስትመንት የትብብር መስኮች ሰፊ ዕድል እንዲኖራት የሚያስችል መሆኑንና ለጀመረቻቸው የልማት ስራዎች ስኬትም ተጨማሪ የፋይናንስ አቅም እንድታገኝ እንዲሁም ወደ ውጭ ለምትልካቸው ምርቶች ሰፊ የገበያ አማራጭ የሚፈጥር መሆኑን በወቅቱ በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት አምባሳደር ሙክታር ከድር (ዶ/ር) መግለጻቸው ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው።
ኢትዮጵያ በቱሪዝም፣ ዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ በኢንዱስትሪ፣ ማዕድንና ግብርና ዘርፎች የጀመረችውን መዋቅራዊ ሽግግር ለማቀላጠፍ ከብሪክስ ተጨማሪ ልምድና ተሞክሮ ታገኝበታለች፤ ልምዷን ለሌሎች ለማካፈልም ምቹ ዕድል ይፈጥርላታል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ብሎም በዓለም ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገቡ ከሚገኙ ሀገራት መካከል ተጠቃሽ ናት። ይህ ደግሞ የብሪክስ አባል ሀገራትን ሰፊ የገበያና የኢንቨስትመንት ዕድል በመጠቀም የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ ዕውን ለማድረግ ተጨማሪ አቅም ይፈጥርላታል። ከዚህም ባለፈ ብሔራዊ ጥቅሟና የሌሎችን የጋራ ተጠቃሚነት መሳ ለመሳ የምታካሂድ ለመሆኗ ትልቅ ማሳያ ነው። ለዚህ ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) 18ኛው የጥምረቱ ጉባኤ ስትራቴጂካዊ ጥቅሞቻችንን ያረጋገጥንበትና የአፍሪካ ድምፅ በዓለም አቀፍ መድረክ ከፍ ብሎ የተሰማበት ታሪካዊ ስኬት ነው ማለታቸው።
ጥምረቱ የደቡብ-ደቡብ ትብብርን ለማሳካት ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል። የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር፣ የአረንጓዴ ኢነርጂ ልማት፣ የምግብ ሉዓላዊነትን በራስ አቅም ማረጋገጥ በትብብሩ ጉልህ ሚና ይኖራቸዋል። ኢትዮጵይ በቀጣናው፣ በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለባትን ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ሃላፊነት ለመወጣት የብሪክስ ማዕቀፍ እና ሌሎችም ዓለም አቀፍ መድረኮች ወሳኝ አጀንዳዎችን ለማራመድ የጎላ ሚና ይኖራቸዋል።
ከብሪክስ ጥምረት በኋላ የተገኙ የዲፕሎማሲና ኢኮኖሚ ስኬቶች
17ኛው የብሪክስ ጉባኤ እ.አ.አ በ2025 በብራዚል ሪዮ ዲጄኔሮ በተካሄደበት ወቅት በዓለም አቀፍ ሰላምና ደህንነት፣ ባለብዙ ወገን ተቋማት ማሻሻያ፣ የአየር ንብረት ፋይናንስ፣ ዓለም አቀፍ ጤና እና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ አጀንዳዎች ላይ መምከሩ ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባኤው ብሪክስ ከጠንካራ አዲስ ሀሳብ ተነስቶ ለዓለም አቀፍ ለውጥ የሚሰራ ብርቱ ኃይል ወደመሆን መሸጋገሩን፤ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የጋራ ደኅንነትን እና ሁሉን አካታች ብልጽግናን ለማምጣት በሚያስችል ሁኔታ አፋጣኝ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚገባቸው፤ በብሪክስ አዳዲስ አባላት መጨመራቸው የጋራ ድምፃችን የበለጠ እንዲጠናከር ያስችላል የጋራ አላማችን የበለጠ ይጠራል። አቅማችንም ይሰፋል ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።
በተጨማሪም እንደ ብሪክስ አባልነቷ ኢትዮጵያ እነዚህ ጥረቶች እንዲሳኩ በተለይም በአለምአቀፍ ውሳኔ ሰጪ መድረኮች ለአዳዲስ ገበያዎች እና በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት ሰፋ ያለ ውክልና በሚገኝበት ሁኔታ ላይ በንቃት አስተዋፅኦ እንደምታደርግ ማንሳታቸው ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ለአፍሪካ ጥቅም መከበር ሚናዋን መቼም የማትዘነጋ መሆኑን አመላካች ነው።
ስለ ዓለም ሰላም፣ የተቀላጠፈ የኢኮኖሚ ሽግግርን በተመለከተ፣ ኢትዮጵያ ለቴክኖሎጂና ፈጠራ እንዲሁም ለቀጣናዊ ውህደት ያላትን ፍላጎትና ቁርጠኝነት በጉልህ ማሳየታቸው፤ ኢትዮጵያ ለቀጣናዊ ልማት፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ብሎም መሰረተ ልማት ዝርጋታና መስፋፋት ያላትን ርዕይ በግልጽ ማንጸባረቃቸው ኢትዮጵያ ለጋራ ሰላም፣ ልማትና ብልፅዕና ያላትን ቁርጠኝነት በግልጽ ያሳየ ነው።
የብሪክስ ጥምረት የዓለም የዲፕሎማሲና የጂኦፖለቲካ ተፅዕኖን ለማሳደግ ካለው ሰፊ ዕድል አንጻር ሲታይም በዓለም አቀፍ መድረኮችና ውሳኔዎች ላይ የሀገሪቱንና የአህጉሪቱን ድምፅ ለማጠናከር ከምዕራባውያን ተፅዕኖ የተላቀቀ ሁለገብ የዲፕሎማሲ ግንኙነትን በጽኑ መሰረት ለመገንባት ወሳኝ ነው።
ኢትዮጵያ በጥምረቱ የምታደርገው ተሳትፎ ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአፍሪካና የሌሎች አህጉራት ታዳጊ ሀገራት በዓለም አቀፍ ባለብዙ ወገን ተቋማት ፍትሃዊ ውክልና ማግኘት እንዳለባቸው በተገኙባቸው ዓለም አቀፍ መድረኮች ሁሉ ሲሞግቱ የሚደመጡትም ይህንኑ የሚያመላክት ነው። ዓለም አቀፍ ውሳኔ ሰጪና የባለብዘዙ ወገን የፋይናንስ ተቋማትንና የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤትን ጨምሮ ማሻሻያ እንደሚያስፈልጋቸው አጽንኦት መስጠታቸውም እንዲሁ። 18ኛው የብሪክስ ጉባኤ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ጥቅሞች መከበር ያለባትን ሀላፊነት በውል እንደምትገነዘብ እና ድምጿን ማስተጋባቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል ያረጋገጠችበት መድረክ ነው።
የብሪክስ ጥምረት ሀገራትን በአባልነት ለማቀፍ ያስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች እና መስፈርቶች የሀገራቱን ዓለም አቀፍ ተፈላጊነትና ተፅዕኖ ፈጣሪነት ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ደግሞ የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ተደማጭነትና ተፅዕኖ ፈጣሪነት በግልጽ አሳይቷል። ኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነትን በተቀላቀለችበት ወቅት ከ40 በላይ ሀገራት ጥምረቱን ለመቀላቀል ፍላጎት አሳይተው ነበር። የአባልነት ጥያቄ ካቀረቡት መካከል ኢትዮጵያን ጨምሮ ስድስት ሀገራት ብቻ መመረጣቸው ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ያላትን ግዙፍ የዲፕሎማሲ ተፅዕኖ ፈጣሪነት ማሳያ ነው።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሳልና አሳታፊ የዲፕሎማሲ ጥረት የተገኘው የብሪክስ ጥምረት አባልነት ባለፉት ጥቂት አስርት ዓመታት ከተመዘገቡ የዲፕሎማሲ ስኬቶች አንፃር ትልቁና አንጸባራቂ ድል ተብሎ ይወሰዳል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥምረቱ የኢትዮጵያን የአባልነት ጥያቄ ሙሉ በሙሉ ተቀብሎ ባጸደቀበት ወቅት እንደተናገሩት የኢትዮጵያ ጥምረቱን መቀላቀል የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲያዊ ልዕልና ማሳያ ነው ሲሉ መግለጻቸውም ይህንኑ ያጠይቃል።
የብሪክስ ጥምረት ኢፍትሃዊውን ዓለም አቀፍ መዋቅርና ሥርዓት ወደ ሚዛናዊ መንገድ በማምጣት በዓለም የፖለቲካ እና የዲፕሎማሲ ውሳኔ አሰጣጥ ላይ ሁሉም ሀገራት ፍትሃዊ ውክልና እንዲኖራቸው ያስችላል። ብሪክስ ይህ ስርዓት መሬት እንዲረግጥ የራሱ አስተዋጽኦ አለው። ለኢትዮጵያም እነዚህ የተዛነፉ ዓለም አቀፍ ባለብዙ ወገን ተቋማት አሰራር ፈር እንዲይዝ የራሷን ሚና ለመወጣትና ዓለም አቀፍ ተፅዕኖዋን ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።
የብሪክስ ጥምረት ውጤት የሆነው የአዲሱ የልማት ባንክ ያለምንም ፖለቲካዊ ቅድመ ሁኔታ ሀገራት መሰረተ ልማት ማስፋፋት የሚችሉበትን ብድር ያቀርባል። ኢትዮጵያም ከሀገር ውስጥ ባለፈ ቀጣናውንና አህጉሪቱን በኤሌክትሪክ ሀይል እና በሌሎች መሰረተ ልማቶች የማስተሳሰር ውጥኗን ዕውን እንድታደርግ ያስችላታል።
ኢትዮጵያ ለጀመረችው መጠነ ሰፊ የመሰረተ ልማት ግንባታ አስተማማኝ የፋይናንስ ምንጭ ይሆናል። እንደ ቻይና፣ ሕንድ እና ሩሲያ ካሉ የዓለምን ኢኮኖሚ ከሚያንቀሳቅሱ ሀገራት ጋር ያላትን የወጭ ንግድና ኢንቨስትመንት ማስፋት፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቷንና የውጭ ምንዛሬ ክምችቷን ማሳደግ፣ የወጪ ንግዷን በራሷ የመገበያያ ገንዘብ ለማከናወን ምቹ ዕድል ይፈጥርላታል። የጥምረቱ አባል ሀገራት በቴክኖሎጂ ውጤቶች ፈጠራ እና የማምረት ብቃትና የተወዳዳሪነት አቅም መጠቀም የሚያስችል የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር ለመፍጠርም በር ከፍቶላታል።
ኢትዮጵያ በ18ኛው የብሪክስ ጉባኤ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ17ኛ የብሪክስ መሪዎች ጉባዔ የአፍሪካን ድምጽ ለዓለም ማሰማታቸው በ18ኛ የብሪክስ ጉባዔ አመርቂ የዲፕሎማሲ ስኬት እንዲመዘገብ አስችሏል። የአፍሪካን ጥቅም ማስጠበቅ፣ የአፍሪካ ህብረት የሰላም ማስከበር ሥራዎች የጎላ ድጋፍ እንዲገኙ፣ ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ጥረት ለውጤት እንዲበቃ የብሪክስ ሀገራት መሪዎች በኒው ዴልሂ ቃላቸውን ሰጥተዋል። የብሪክስ ሀገራት በአዲሱ የልማት ባንክ የአባልነት ጥያቄያቸው በፍጥነት እንዲታይ፣ በታዳጊ ሀገራት መካከለ ዘላቂ የዕዳ አስተዳደር ስምምነቶች እንዲኖሩ በማድረግ ኢትዮጵያ ገንቢ ሚና ተጫውታለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ18ኛው የብሪክስ ጉባኤ የኢትዮጵያን ውጤታማ ስኬቶች በጉልህ አንስተዋል። ኢትዮጵያ ከውጭ ከሚገባ የስንዴ ጥገኝነት ተላቃ በምግብ ራሷን መቻሏን፣ በቅድመ መከላከል የጤና ፖሊሲ ውጤት ማስመዝገቧን፣ የህክምና ቁሳቁሶችና መድኃኒቶች በሀገር ውስጥ በማምረት አክሞ የማዳን አቅሟን ማሳደጓን፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ደህንነቱ የተጠበቀ አጠቃቀምና ሽግግር መፍጠሯን፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም አዳጊ ፍላጎቶችን ሊያሳካ የሚችለውን የመደመር ሰው ሰራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ ግንባታን በማንሳት ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ትብብርና ልማት ያላትን ቀናኢነት አንስተዋል። የዲጂታል ቴክኖሎጂና ሰው ሰራሽ አስተወሎት ያመጣቸው ዕድሎችን መጠቀምና ስጋቶችን ለመፍታት ከብሪክስ አባል ሀገራት ጋር መሥራት አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው መናገራቸውም ይታወሳል።
አፍሪካ ጠንካራ ውክልና እንዲኖራት፣ የፋይናንስ እና የገበያ ተደራሽነት ይበልጥ እንዲሰፋ፤ ንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ትስስርን ለማሳደግ ተግባራዊ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ ያቀረቡበት መድረክ ነበር። አዲሱ የልማት ባንክ በመላው አፍሪካ አድማሱን በማስፋት በአዲስ አበባ ቢሮውን እንዲከፍት የጠየቁበት፤ ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ በሙሉ አቅም ዝግጁ መሆኗን ማረጋገጣቸው፣ በአጠቃላይ 18ኛ የብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ጥቅሞች መከበር ፊት አውራሪነቷን በድጋሚ ያረጋገጠችበት ሆኖ ተጠናቋል።
እንደ መውጫ
ኢትዮጵያ ከፍተኛ የመልማት አቅም ያላት ሀገር ናት። ለያዘቻቸው የልማት ርዕዮች መሳካት አማራጭ የፋይናንስ ምንጮች ያስፈልጓታል። ለዚህ ደግሞ ብሄራዊ ጥቅሟን ያስከበረና ሚዛናዊነቱን የጠበቀ የዲፕሎማሲ ስኬት እያስመዘገበች በልዩ ጥንካሬ ወደፊት እየገሰገሰች ትገኛለች። በታሪካዊው 18ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ የተገኘውን ወርቃማ የዲፕሎማሲ ድል ወደ ዘላቂ ልማት ለመቀየር የተቀናጀ ጥረት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ የመንግሥት ተቋማት፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ ወጣቶች እና ታዋቂ ግለሰቦች የጋራ ሀገራዊ ራዕይ በመሰነቅ፣ ብሄራዊ አንድነትንና ጥንካሬን በማንገብ ለኢትዮጵያ ዕድገትና ብልጽግና በቁርጠኝነት መሰለፍ ይገባቸዋል።