ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል በሚቀጥሉት ወራት መደበኛና ከመደበኛ በላይ የዝናብ ስርጭት ይጠበቃል

ጋምቤላ ፤መስከረም 8/ 2018 (ኢዜአ) ፡-በጋምቤላ ክልል በሚቀጥሉት ወራት መደበኛና ከመደበኛ በላይ የዝናብ ስርጭት ሊኖር እንደሚችል በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዮት የጋምቤላ ክልል የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል አስታወቀ።

በክልሉ የሚኖረው  የዝናብ ስርጭት  ለእርሻ ስራ አወንታዊ ሚና እንዳለው ሁሉ ቅጽበታዊ ጎርፍ በመፍጠርም አሉታዊ ተጽኖ ሊኖረው እንደሚችል ማዕከሉ ገልጿል።

የማዕከሉ መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ተስፋሁን ዓለሙ ለኢዜአ እንደገለጹት ከተያዘው መስከረም አጋማሽ ጀምሮ በቀጣዮቹ ወራት መደበኛና ከመደበኛ በላይ  የዝናብ ስርጭት ሊኖር እንደሚችል የአየር ትንበያ መረጃዎች ያመለክታሉ ።

በክልሉ በተለይም በጥቅምትና ህዳር 2019 ዓም  መደበኛና ከመደበኛ በላይ ጠንከር ያለ የዝናብ ስርጭት  እንደሚኖር ገልጸዋል።

በክልሉ ሊኖር የሚችልው የዝናብ ስርጭት ዘግይተው ለሚዘሩና ለረጅም ጊዜ ሰብሎች አመች ሁኔታ እንደሚኖረው ተናግረዋል። 

እንዲሁም ለበጋ የግብርና ልማት ስራዎች እርጥበታማ አፈርን በመፍጠርና የውሃ አቅሞችን በማሳደግ ረገድ አዎንታዊ አስተዋፆ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

በአንፃሩ የክልሉ መልከአ ምድራዊ አቀመማጥ ዝቅተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በአጎራባችና በአካባቢው የሚጥለው ጠንክር ያለ ዝናብ የጎርፍ አደጋ ሊያስከትል ይችለል ብለዋል።

በተለይም ባሮን ጨምሮ ክልሉን አቋርጠው የሚያልፉ አራት ታላላቅ ወንዞች ሞልተው በመፍሰስ ለጎርፍ ሊያጋልጡ ስለሚችሉ በወንዞች አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ ምክረ ሃሳብ ለግሰዋል።

በተጨማሪም የዝናቡ ስርጭት ለወባ ትንኝ መራባት ምቹ ሁኔታን ስለሚፈጥርና የወባ በሽታ ሊጨምር ስለሚችል አስፈላጊው ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ  አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም