ቀጥታ፡

"ጊፋታ"- ከጅምሩ እስከ ጋዜ ኦሩዋ

(በማስረሻ ሀብታሙ ከኢዜአ ወላይታ ሶዶ ቅርንጫፍ)

የወላይታ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል "ጊፋታ" ሕዝቡ ለዘመናት ሲያከብረው የኖረ ደማቅ ባህላዊ እሴት ነው፡፡ ጊፋታ የተጣሉና የተኮራረፉ የሚታረቁበት እንዲሁም የሕዝቦች አንድነትና አብሮነት ይበልጥ የሚጠናከርበት የወላይታ ዘመን መለወጫ በዓል ነው፡፡ ጊፋታ አዲስ ተስፋና ብርሃን ጭምር ነው፡፡ አሮጌው አልፎ አዲሱን ዘመን በአዲስ መንፈስና መነሳሳት የሚቀበሉበት በጉጉት የሚጠበቅ በዓል ነው፡፡ ጊፋታ ለአብሮነትና ለሰላም እንዲሁም ለልማትና ብልጽግና በመዘጋጀት የሚቀበሉት ልዩ በዓልም ነው፡፡ በዓሉ ማኅበረሰቡ ሁለንተናዊ የሕይወት ዑደትን የሚማርበት፣ ከትናንት በመማር ለነገ የሚዘጋጅበት፣ የአብሮነትና የትስስር እሴት ነው፡፡


 

ያነጋገርናቸው የወላይታ ባህል፣ ታሪክና ቅርስ ባለሙያ አቶ አዳነ አይዛ እንደሚሉት፤ ጊፋታ ታላቅ፣ በኩር፣ የመጀመሪያ፣ መሻገር የሚል ትርጓሜ አለው፤ ይህም ከአሮጌ ወደ አዲስ፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን መሻገርን የሚያሳይ ነው። ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣው ይህ በዓል በወላይታ ባህላዊ የጊዜ አቆጣጠር የመጀመሪያው ወር መሆኑን ያብራራሉ።

ዕለቱም የጨረቃንና የፀሐይን እንቅስቃሴ መሰረት ያደረገውን የወላይታዎች ባህላዊ የጊዜ አቆጣጠርን በመከተል የሚከበር መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡ ረጅም የመዘጋጃ ጊዜን የሚወስደው የጊፋታ በዓል ከአባቶች እስከ ሕፃናት በበዓሉ ዝግጅት ላይ የየራሳቸው የሥራ ድርሻ ያላቸው ሲሆን፤ የቅድመ ዝግጅት ሥራው በአብዛኛው በደቦ ይከወናል። በዓሉ በሚቃረብበት ወቅት ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል እርቅ ዋናው መሆኑን የሚገልጹት ባለሙያው፤ በዚህ ወቅት የተጣሉ ሰዎች እርስ በርሳቸው ታርቀው እና ጥላቻን ረስተው የጊፋታን በዓል እንደሚያከብሩ አውስተዋል፡፡ የተበደሩትን ዕዳ መክፈል ሌላኛው የጊፋታ በዓል ቅድመ ዝግጅት እንደሆነ እና ዕዳን ሳይከፍሉ ጊፋታን ማለፍ የተወገዘ ተግባር እንደሆነም አመልክተዋል፡፡

ጊፋታ ከመድረሱ ሦስት ወር ቀደም ብሎ ከአሮጌው ዓመት ጉሌ ወር ላይ ወጣቶች ተሰባስበው በአካባቢው የወደቁና ከጥቅም ውጭ የሆኑ እንጨቶችን በመልቀም በአንድ ቦታ ላይ በማከማቸት በዓሉን በእሳት ብርሃን እንደ ወደፊት ተስፋ በመውሰድ ያከብራሉ፡፡ እንዲሁም በዓሉ ሲቃረብ የመታደስ ምልክት የሆነውን አካባቢያቸውን የማጽዳት ሥራ የሚያከናውኑ ሲሆን፤ መኖሪያ ቤታቸውን የማሳደስና የተለያዩ ያረጁ ቁሶችን በአዲስ የመተካት ተግባር ያከናውናሉ፡፡


 

በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና ቅርስ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ አበሻ ሺርኮ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በዓሉ የሁለት ወር ጊዜ ሲቀረው አባወራዎች የእርድ በሬ በመግዛት ለተመረጠ ቤተሰብ በማስረከብ ከብቱ እንዲደልብና በደረቅ የኮባ ቅጠል በተሸፈነ ልዩ በረት በልዩ እንክብካቤ እንዲቀለብ ያደርጋሉ። 

በጊፋታ በዓል ዝግጅት አባቶችና ታላላቅ ወንድ ልጆች የጉሊያ እንጨት በማሰባሰብ፣ ማቆምና የማገዶ እንጨት መፍለጥ፣ ቆጮ መቁረጥ እና ሌሎችንም ሥራዎች ይሠራሉ። እናቶች እና ሴት ልጆቻቸው ደግሞ ለተለያዩ ባህላዊ ምግቦች እንሰትን መፋቅ፣ የማሽላና የበቆሎ ዱቄት፣ ዳጣ በርበሬ የማዘጋጀት፣ የተለያዩ ባህላዊ መጠጦችን እንደ ቦርዴና ጠላ ያሉትን በትላልቅ እንስራ ያዘጋጃሉ። 

የጊፋታ በዓል የሚከበርበት የአዲሱ ዘመን የመጀመሪያ ቀን ከሆነው እና እርድ ከሚከናወንበት የእሑድ ቀን በፊት ቅዳሜ (በወላይታ አቆጣጠር የአሮጌው ዓመት መጨረሻ ቀን) ላይ ሁሉም ሰው ንጽሕናውን የመጠበቅ ሥራ ያከናውናል፡፡ ይህ የሚደረገውም ከአሮጌው ዓመት እድፍና ቆሻሻ ጋር ወደ አዲሱ ዓመት መሻገር አያስፈልግም በሚል ነው፡፡

የእርድ ዕለት እሑድ (የወላይታ ዘመን መለወጫ) ጠዋት ወፎች ዜማቸውን እንዳሰሙ የእርድ ተግባሩ መከናወን ይጀምራል፤ በዚሁ ወቅትም እናቶች ያዘጋጁት መጠጥ እና ምግብ በእርዱ ለሚሳተፉት ሰዎች ይቀርባል። አባወራዎች ሥጋውን ተከፋፍለው ወደ ቤታቸው ከመውሰዳቸው በፊት ሁሉም በአንድ ላይ ይበላሉ፤ ይጠጣሉ። ይህም ፍቅራቸውን ከአንድ ማዕድ በመቁረስ የሚያድሱበትና አዲሱን ዓመት የሚያበስሩበት እንደሆነ አበሻ (ዶ/ር) ይገልጻሉ።

በቀጣይም ዕጣ በመጣጣል ሥጋውን ተከፋፍለው ለጊፋታ ተብሎ በሚገዛ አዲስ ቅርጫ ሥጋውን ይዘው ወደ ቤታቸው እንደሚወስዱ እና እናቶች በቤት ውስጥ የመጣውን ሥጋ ባልተበሳሳ ኮባ ቅጠል ላይ ዙሪያውን በማስቀመጥ በቆጮ፣ በቂጣ፣ በዳጣ በርበሬ አድርገው ሲያቀርቡ፤ አባት ደግሞ እማወራዋን በማጉረስ እንደሚጀምሩ ያስረዳሉ።


 

በጉሊያ ወር በወጣቶች የተሰበሰበው እንጨት (ጉሊያ) ለጊፋታ በዓል ሁለት ሳምንት ሲቀረው እንዲቆም የሚደረግ ሲሆን፤ በዕለቱ አመሻሽ ላይ ሁሉም በተሰበሰቡበት አባወራው ጉሊያውን በእሳት ይለኮሳሉ፡፡ ወጣቶችም ዙሪያውን በመክበብ ባህላዊ ጭፈራ ይጨፍራሉ። በቀጣዩ ቀንም በቤት ውስጥ የተረፈው ሥጋ ተዘልዝሎ ይጠበስና ማባያ ተዘጋጅቶ ሁሉም ተሰብስበው በመመገብና በመዝናናት በአንድነት ያሳልፋሉ።

ከጊፋታ ቀጥሎ የሚመጣው ሦስተኛው ቀን ወይም ጪሻ ጋላሳ ደግሞ በጊፋታ ወቅት ብቻ የሚፈካ፣ በወላይታዎች አባባል ኮርማ-ጪሻ የሚባለውን ነጭ አበባ ወይም የጊፋታ አበባ ይዞ በመሄድ ዘመድ የሚጠያየቅበት ዕለት ይሆናል።

ከጊፋታ ሦስተኛው ቀን ጀምሮ ደግሞ በተከታታይ ለሁለት ሳምንታት ወጣት ወንዶችና ወጣት ሴቶች በአካባቢው ታዋቂ ሽማግሌ ደጃፍ ተሰብስበው በጋዚያ ጨዋታ ያሳልፋሉ፡፡ ይህም ጋዜ ኦሩዋ በመባል ይታወቃል። ለረጅም ጊዜ የቆየው የበዓል ዝግጅትና አጠቃላይ የጊፋታ በዓል ሥነ ሥርዓት የጋዜ ኦሩዋ ጨዋታ ሲጠናቀቅ ጉሊያ በማቀጣጠል ለሚመጣው ዓመት በዓል በሰላም እንዲያደርሳቸው በመመኘት ይሸኛሉ።


 

ታዲያ ይህ የወላይታ ብሔር አዲስ ዓመት በዓል የሆነው "ጊፋታ" በ2018 ዓ.ም ታኅሣሥ ወር ላይ በሕንድ ሀገር ኒው ዴልሂ ከተማ በተካሄደው በ20ኛው የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ ጥበቃ የመንግሥታት ኮሚቴ ስብሰባ ላይ በሰው ልጆች ወካይ ቅርስነት በተባበሩት መንግሥታት ትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ተመዝግቧል። በዓሉ ዕድሜ፣ ጾታ፣ ሃይማኖትና ማኅበራዊ ደረጃን ሳይለይ የሚያሳትፍ መሆኑ፣ ቅርሱ ተላልፎ ጥሩ ደረጃ ላይ የሚገኝ በመሆኑ እንዲሁም በትምህርት ቤቶችና በሚዲያዎች ለትውልድ በመሸጋገር ላይ የሚገኝ መሆኑ እና ሌሎች መመዘኛዎችን በማሟላቱ ነው በዩኔስኮ መመዝገብ የቻለው።

"ጊፋታ" የዓለም ሕዝብ ሀብት ሆኖ በዩኔስኮ ከተመዘገበ በኋላ የሚከበረው የዘንድሮ መርሃ ግብር በወላይታ ዘመን አቆጣጠር መሰረት የወላይታ ዘመን መለወጫ ወይም "ጊፋታ 1" ወይም በኢትዮጵያ አቆጣጠር መስከረም 10 ቀን 2019 ዓ.ም  በድምቀት ይከበራል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም