ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በዘርፉ ልማት በጥሩ ተሞክሮነት የሚወሰድ ነው- የውጭ ሀገራት ተመራማሪዎች

ሀዋሳ፤ መስከረም 8/2019 (ኢዜአ) :- የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አስደናቂና በዘርፉ ልማት በጥሩ ተሞክሮነት የሚወሰድ መሆኑን የተለያዩ ሀገራት የደን ዘርፍ ተመራማሪዎች ገለጹ።

ኢትዮጵያ ባለፉት ስምንት ዓመታት በድምሩ 56 ነጥብ 2 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል በዘርፉ ልማት የመሪነት ሚናዋን አጠናክራ ቀጥላለች።

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ባለፈ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ ለምግብ ዋስትናም መሰረት እያኖረ መሆኑ ይታወቃል።

በመሆኑም የኢትዮጵያን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በተመለከተ ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ ሀገራት የዘርፉ ባለሙያዎች፤ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ትልቅ ስኬት የተመዘገበበት አስደናቂ የልማት ስራ መሆኑን ገልጸዋል።

ኒዘርላንዳዊው የዘርፉ ተመራማሪ  አልበርት ስቼንክ፤ ኢትዮጵያ የዓለም ፈተና የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ በመካላከል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገች መሆኑን በተግባር እያሳየች መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አስደናቂና በዘርፉ ልማት በጥሩ ተሞክሮነት የሚወሰድና ሁሉም ሊደግፈው የሚገባ መልካም ተግባር መሆኑን አንስተዋል።

የአየር ንብረት ለውጥን የመከላከል ጉዳይ የሁሉም ሀገራት የጋራ ሃላፊነት መሆኑን የተናገሩት ተመራማሪው ሀገራት የኢትዮጵያን ፈለግ መከተል ይገባቸዋል ብለዋል።

የተፈጥሮ ሀብትና ደንን ለመንከባከብ የሚደረግ ጥረት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚን ለመገንባት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው በአረንጓዴ ልማት ላይ የሚውል ጉልበትና ገንዘብ መልሶ የሚከፍል ሀብት በመሆኑ ሊተኮርበት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ሌላኛው ኡጋንዳዊው የደን ሃብት ልማት ተመራማሪ ሮበርት አቱጎንዛ፤ በደን ልማትና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ኢትዮጵያ ትልቅ እቅድ ሰንቃ እየሰራችና በተግባርም እያሳየች ትገኛለች ብለዋል። 


 

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ልማት የዓለም ፈተና የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ የመከላከል ጥረት፣ የተፈጥሮ ሃብትን የመጠበቅና የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ መሰረት ሆኖ መቀጠሉ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል። 

በመሆኑም የአፍሪካ ሀገራት በተለይም የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ከኢትዮጵያ ልምድ በመቀመር በተባበረ አቅም የልማት ስራውን ማስቀጠል ይኖርባቸዋል ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል።

በታንዛኒያ የደን ጥበቃ ፕሮግራም አስተባባሪና የደንና የተፈጥሮ ሀብት ተመራማሪ አልማስ ካሽንዲዬ፤ በኢትዮጵያ የችግኝ ተከላ እና እንክብካቤ ስራ የህዝብ አጀንዳ ሆኖ የቀጠለ አስደናቂ መርሃ ግብር ነው ሲሉ ተናግረዋል።


 

የተፈጥሮ ሀብትን መጠበቅና መንከባከብ የብዝሃ ህይወትንና የውሃ አካላትን መጠበቅ፤ የአየር ንብረት ለውጥን የመከላከልና የምግብ ዋስትና መሰረት በመሆኑ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው ሲሉ አስረድተዋል።

የዘርፉ ምሁር የሆኑት ቦሊቪያዊው ሁምቤርቶ ጎሜዝ፤  ኢትዮጵያውያን ባለፉት ስምንት ዓመታት የተከሏቸው ችግኞች በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተከናወነ ላለው የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ትልቅ ትርጉም ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል።


 

በመሆኑም ኢትዮጵያና ዜጎቿ በአረንጓዴ አሻራ ልማት እያደረጉት ላለው አስተዋጽኦ የላቀ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም