ሀገር የሚገነባው እያንዳንዱ ዜጋ የራሱን ድርሻ ሲወጣ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሀገር የሚገነባው እያንዳንዱ ዜጋ የራሱን ድርሻ ሲወጣ ነው
አዲስ አበባ ፤ መስከረም 8/2019(ኢዜአ) :- ዛሬ ላይ የምንሰራው የበጎ ፈቃድ ተግባር የዜጎችን ችግር ከመፍታት ባሻገር ለነገው ትውልድ የመተባበርና የመረዳዳት ባህልን ይተክላል ሲሉ በብልጽግና ፓርቲ የሀረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ ገለጹ።
ጽሕፈት ቤቱ በክልሉ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትን በገመገመበት ወቅት ኃላፊው እንደተናገሩት 209 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸውና የዜጎችን ችግር ያቃለሉ የበጎ ፈቃድ ተግባራት በክልሉ ተከናውነዋል።
ሀገር የሚገነባው እያንዳንዱ ዜጋ የራሱን ድርሻ ሲወጣ ነው ያሉት አቶ ጌቱ አንድ ወጣት ጊዜውን ሲሰጥ፣ አንድ ባለሙያ እውቀቱን ሲያካፍል፣ አንድ ዜጋ የተቸገረን ወገን ሲደግፍ፣ አንድ ሰው አካባቢውን ሲያፀዳ ወይም ችግኝ ሲተክል በተደመረ ውጤት የሀገር ግንባታ እንደሚሆን አስረድተዋል።
በዚህ መርህ የምንከውነው የክረምት በጎ ፈቃድ ተግባር የአንድ ወቅት ዘመቻ ብቻ ሳይሆን፣ በመረዳዳትና በመተባበር የሀገር ፍቅርን በተግባር የምናሳይበት መድረክ ነው ብለዋል።
ወጣቶች፣ ባለሙያዎች፣ ተማሪዎች፣ የሀገር አገልጋዮችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና እውቀታቸውን ለማህበረሰብ እያበረከቱ መሆኑንም ገልጸዋል።
የምንሰራው በጎ ተግባር ዛሬ ላይ የዜጎችን ችግር ከመፍታት ባሻገር ለነገ ትውልድ የመተባበርና የመረዳዳት ባህልን የሚተክል በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
በአንድነት የጀመርነውን የክረምት በጎ ፈቃድ ተግባር በክረምት ሳንገድበው በየቀኑ በየቦታው የምንኖረውን የመረዳዳት ባህል እንገንባ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።