ቀጥታ፡

በቡና የወጭ ንግድ የተመዘገበውን አበረታች ስኬት በቅመማ ቅመም መድገም የሚያስችል የምርታማነት አቅም እየተፈጠረ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 8/2019 (ኢዜአ):-በቡና የወጭ ንግድ የተመዘገበውን አበረታች ስኬት በቅመማ ቅመም ዘርፍም መድገም  የሚያስችል የምርታማነት አቅም እየተፈጠረ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን አስታወቀ።             

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ የቅመማ ቅመም ዘርፉን ስልታዊ በሆነ መንገድ ለማዘመን አጠቃላይ ጥረቶች መጀመራቸውን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ሮዝመሪ፣ ኮረሪማ፣ ጥቁር አዝሙድ እና ዝንጅብልን ጨምሮ 16 የተለያዩ የቅመማ ቅመም ዓይነቶች ለውጭ ገበያ እየቀረቡ ይገኛሉ።

ባለፈው የበጀት ዓመት ብቻ ከዚህ ዘርፍ 17 ሚሊዮን ዶላር ገቢ የተገኘ ሲሆን፣ አሁን ላይ ይህንን አፈጻጸም ወደ 20 ሚሊዮን ዶላር ለማሳደግ ታቅዶ እየተሠራ ነው።

ለእነዚህ 16 የቅመማ ቅመም ዓይነቶች የሚሆን ዘመናዊ የአመራረት፣ የጥራት አጠባበቅ እና የገበያ ሥርዓት ፓኬጆች ተዘጋጅተዋልም ብለዋል።

እነዚህን አዳዲስ ፓኬጆች ወደ መሬት ለማውረድ የሚያስችሉ ዝርዝር መመሪያዎችም መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ተግባራዊነቱን ውጤታማ ለማድረግም በአርሶ አደሮች እና በግብርና ባለሙያዎች ላይ ያተኮረ ሥልጠና መሰጠቱን ጠቅሰዋል።

በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቀጠል የምርት ጥራት ወሳኝ በመሆኑ ጥብቅ የቁጥጥር ሥርዓቶች እየተዘረጋ ይገኛል ብለዋል።

በዚህ ረገድም ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ጋር በምርት ጥራት ቁጥጥር ዙሪያ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የትብብር ስምምነት መፈረሙን አስታውቀዋል።

አሁን ላይ በዓመት የሚመረተው የቅመማ ቅመም መጠን 10 ሺህ ቶን የደረሰ ሲሆን፣ ይህንን ወደ 13 ሺህ ቶን ከፍ ለማድረግና መዳረሻ ገበያዎችን ለማስፋት ግብ ተይዞ እየተሠራ ነው ብለዋል።

በድህረ ምርት ዙሪያ ለአርሶ አደሮች በፓኬጅ የተደገፉ ሥልጠናዎች ተደራሽ እየተደረጉ መሆኑ የምርት ጥራትን ለማረጋገጥ ዓይነተኛ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል።

እነዚህ የተቀናጁ ጥረቶች የኢትዮጵያን የቅመማ ቅመም ምርቶች ተወዳዳሪነት በማሳደግ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ገቢ ከፍ እንደሚያደርጉት ይጠበቃልም ነው ያሉት።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም