የዘንድሮው የኢሬቻ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ መስከረም 21 ቀን በቢሾፍቱ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የዘንድሮው የኢሬቻ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ መስከረም 21 ቀን በቢሾፍቱ ይካሄዳል
ቢሾፍቱ፤ መስከረም 8/2019 (ኢዜአ) ፡-የዘንድሮውን የኢሬቻ በዓል ምክንያት በማድረግ መስከረም 21 ቀን በቢሾፍቱ ከተማ ለሚካሄደው የጎዳና ላይ ሩጫ አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን የኦሮሚያ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ።
የኦሮሚያ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የ2019 ዓ.ም የ2ኛውን የኢሬቻ የጎዳና ላይ ሩጫ ዝግጅት አስመልክቶ በዛሬው ዕለት በቢሾፍቱ ከተማ ሆራ አርሰዴ አዳራሽ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥቷል።
በመግለጫው ላይ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ አባ ገዳዎችና ታዋቂ አትሌቶች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን፤ በዓሉ የባህል እሴትን ከስፖርት ጋር በማጣመር በደመቀና በተዋበ ሁኔታ እንዲከበር የሚያስፈልጉ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸው ተገልጿል።
የኦሮሚያ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሮዛ ቢያ እንደገለጹት፤ የኢሬቻ በዓል እና የስፖርት እንቅስቃሴዎች የባህል ዕሴቶችን ለማበልጸግ፣ ፍቅርና ወንድማማችነትን ለማጠናከር እንዲሁም አገራዊ ኢኮኖሚን ለማጎልበት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው።
አክለውም፣ ኢሬቻ የህዝቦችን አንድነት እና ፍቅር በማጽናት በሀገር አቀፍ ደረጃ ዘላቂ ሀገራዊ መግባባትን ለመገንባት ጉልህ ሚና እንደሚጫወት አብራርተዋል።
በዘንድሮው የ2ኛው የኢሬቻ ሩጫ ውድድር እስከ 6ኛ ደረጃ ለሚያጠናቅቁ አትሌቶች ልዩ ልዩ ሽልማት የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸው፤ በተጨማሪም የዲባባ ቤተሰቦች የኢሬቻ ሩጫ አምባሳደር መሆናቸውን ገልጸዋል።
ቢሮውም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የ2019 የኢሬቻ በዓልን በታላቅ ቅንጅት ለማክበር ከሚያደርጋቸው ዝግጅቶች መካከል አንዱ 2ኛው የኢሬቻ ታላቅ ሩጫ መሆኑንም አብራርተዋል።
የጎዳና ላይ ሩጫው ዋና ዓላማ የኢሬቻ በዓል ባህላዊና ሥነ-ምግባራዊ እሴቱን ጠብቆ ከማከበር ጎን ለጎን ከስፖርት ጋር በማያያዝ ለተከታዩ ትውልድ ለማስተላለፍና የህዝቡን ባህል ለዓለም ለማስተዋወቅ ያለመ መሆኑንም ገልጸዋል።
የቱለማ አባ ገዳ ጌቱ ተሊላ በበኩላቸው፤ ኢሬቻ ፍቅርና አንድነት በመሆኑ፣ በበዓሉ ምክንያት የተዘጋጀው ሩጫም ፍቅርን፣ አንድነትንና የብሔር ብሔረሰቦችን ቁርኝት ስለሚያጠናክር ህዝቡ እንዲሳተፍ ጥሪ አድርገዋል።
ውድድሩ በስኬት እንዲጠናቀቅ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ድርሻቸውን እንዲወጡና ህዝቡ በሰላም መጥቶ በሰላም እንዲመለስ በቅንጅት እየተሠራ መሆኑም አመልክተዋል።
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ስማቸውን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያስጠሩት የዲባባ ቤተሰቦች የኢሬቻ ሩጫ አምባሳደር ሆነው ተመርጠዋል።
አትሌቶች በአምባሳደርነታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፣ ውድድሩን በስፋት ለማስተዋወቅ በቁርጠኝነት እንደሚሠሩም አረጋግጠዋል።
ውድድሩ 10 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚሸፍን የህዝብ ሩጫ ሲሆን የኬንያ እና የታንዛኒያ አትሌቶችን ጨምሮ በሁለቱም ጾታ አትሌቶችም ይሳተፉበታል ተብሏል።