በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአደባባይ በዓላትን ያለምንም ችግር ለማክበር የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል-ፖሊስ - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአደባባይ በዓላትን ያለምንም ችግር ለማክበር የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል-ፖሊስ
ወላይታ ሶዶ፤ መስከረም 8/2019 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአደባባይ በዓላትን ያለምንም ችግር ለማክበር የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
በኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነርና የወንጀልና የትራፊክ አደጋ መከላከል ዘርፍ ኃላፊ ኮማንደር ደግፌ ደበላ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በቀጣይ ቀናት የሚከበሩ ሕዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላት ያለምንም ችግር እንዲከበሩ የተሟላ ዝግጅት ተደርጓል፡፡
በክልሉ በቀጣይ ቀናት በወላይታ ጊፋታ፣ በጋሞ ዮ ማስቃላ፣ በጎፋ ጋዜ ማስቃላ እና በሌሎችም አካባቢዎች የአደባባይ በዓላት እንደሚከበሩም ገልጸዋል።
በክልሉ በአደባባይ ለሚከበሩ በዓላት ሰላማዊ ክንውን ግብረ ኃይል ተቋቁሞ የተሟላ እና የተቀናጀ ስምሪት ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
የትራፊክ እንቅስቃሴን ከማሳለጥ ጀምሮ በዓላቱ በሚከበሩባቸው አካባቢዎች የጸጥታ ቁጥጥርና ጥበቃ ሥራዎች በተጠናከረ ሁኔታ ማከናወን በሚያስችል መልኩ ዝግጅት መደረጉን አስረድተዋል።
በግብይት ወቅት ሕብረተሰቡ ከሐሰተኛ ገንዘብ ስርጭት እና ባዕድ ነገሮችን ቀላቅለው ከሚሸጡ ህገወጦች ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበትም ጠቁመዋል።
አሽከርካሪዎችም የትራፊክ አደጋን በመከላከል የሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው በአፅንኦት ተናግረዋል።
ሕብረተሰቡ ከመደበኛ እንቅስቃሴ የተለየ ነገር ሲመለከት እና የወንጀል ሥጋቶች ሲኖሩ በአቅራቢያ ለሚገኝ ፖሊስ ጥቆማ በመስጠት ሊተባበር እንደሚገባም አመልክተዋል።