ቀጥታ፡

የሶማሌ ክልልን ሕዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ፕሮጀክቶች በብቃትና በጥራት እየተፈጸሙ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 8/2019 (ኢዜአ):- የሶማሌ ክልልን ሕዝብ ሁለንተናዊ  ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ፕሮጀክቶች በብቃትና በጥራት እየተፈጸሙ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።

አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር በፌዴሬሽን ምክር ቤትና ተጠሪ ተቋማት በሶማሌ ክልል ጎዴ ከተማ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የተገነቡ መኖሪያ ቤቶችን ለተጠቃሚዎች አስረክበዋል።

አፈ ጉባዔው በዚሁ ወቅት፤ ለአቅመ ደካሞች የተገነቡት የመኖሪያ ቤቶች ዜጎች የነበረባቸውን የቤት ችግር በመቅረፍ አስተማማኝ መጠለያ እንዲኖራቸው የሚያደርግ ነው ብለዋል።

ፌዴሬሽን ምክር ቤትም በክልሉ ከአቅመ ደካማ ወገኖች የቤቶች ግንባታ በተጨማሪ ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ በማቅረብ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

እንዲሁም በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር አካባቢን በመጠበቅ ለቀጣይ ትውልድ የሚጠቅም መሠረት በመጣል የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አንስተዋል።

የሶማሌ ክልል በመደመር መንግሥት የአስተዳደር ሁለንተናዊ  ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ የልማት ፕሮጀክቶች እውን የሚሆኑበት ዕድል መፈጠሩን ተናግረዋል።

በዚህም የክልሉን ሕዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ በርካታ የልማት ፕሮጀክቶች ተገንብተው የሕዝብን የልማት ጥያቄ በመመለስ ለአገልግሎት መብቃታቸውን አስረድተዋል።

ለአብነትም በማኅበራዊ ዘርፍ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል የጤና ተቋማት ግንባታን በማስፋፋት ሕብረተሰቡ በአቅራቢያው የሕክምና አገልግሎት የሚያገኝበት ዕድል መፈጠሩን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም በመንገድ፣ በአየር ማረፊያ መሠረተ ልማቶችና በኢንቨስትመንት ፍሰት የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ድሎች መመዝገባቸውን አብራርተዋል።

የመደመር መንግሥት የልማት ፕሮጀክቶችን በጥራትና በፍጥነት ጀምሮ ማጠናቀቅ ዋነኛ መለያው መሆኑን በመጥቀስ፤ ይህም የክልሉን ሕዝብ ተጠቃሚነት እያሻሻለ መሆኑን አብራርተዋል።

የሶማሌ ክልል ሕዝብ ለዘላቂ ልማትና ሰላም ያለው ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው ያሉት አፈ ጉባዔ አገኘሁ፤ በቀጣይም ቀጣይነት ያለው ሰላምና ልማት የማረጋገጥ ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ከተጠሪ ተቋማት ጋር በጋራ በመሆን ሕብረ ብሔራዊነትን በማጠናከር በልማት ሥራዎች ያለውን ተሳትፎ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም