ቀጥታ፡

መሶብ የአንድ ማዕከል ተንቀሳቃሽ አገልግሎት መንግስት ለህዝብ የሰጠው ፈጣንና ቁርጠኛ ምላሽ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 8/2019 (ኢዜአ):- መሶብ የአንድ ማዕከል ተንቀሳቃሽ አገልግሎት መንግስት ለህዝብ የሰጠውን ፈጣን እና ቁርጠኛ ምላሽ በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን ተገልጋዮች ገለጹ።

መንግስት በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት ባደረገው ጥረት ቀልጣፋ እና ዘመናዊ ተቋማትን በመገንባት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል።

ለዚህም ማሳያ የሆነው የመሶብ አገልግሎት እጅግ ፈጣን እና ቀልጣፋ በመሆኑ በዜጎች ዘንድ ትልቅ እርካታን ፈጥሯል።

በተለይም የተንቀሳቃሽ መሶብ አገልግሎት ነዋሪዎች ወደ መንግስት ተቋማት መሄድ ሳይጠበቅባቸው ባሉበት አካባቢ ሆነው ጉዳያቸውን በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲፈጽሙ ምቹ ሁኔታን መፍጠር የቻለ ነው።

የተንቀሳቃሽ መሶብ አገልግሎት በአካባቢያቸው ሲያገኙ ኢዜአ ያነጋገራቸው የመዲናዋ ነዋሪዎችም መንግስት ቀደም ሲል ይስተዋሉ የነበሩ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በፍጥነት መቅረፉ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል። 

ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል አቶ ታምሩ አሰፋ እንደገለጹት፤ ቀደም ሲል ይሰጥ የነበረው የመንግሥት አገልግሎት ረጅም ጊዜ የሚወስድና ለእንግልት የሚዳርግ እንደነበር አስታውሰዋል።


 

አሁን ላይ አሠራሩ እጅግ ዘመናዊ በመሆኑ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት ማግኘት መቻላቸውን ገልጸዋል።

በተለይ የተንቀሳቃሽ መሶብ አገልግሎት በመኖሪያ አካባቢዎቻቸው የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት መቻሉ የበለጠ እርካታ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።


 

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ታምራት ከበደ በበኩላቸው፤ የተንቀሳቃሽ መሶብ አገልግሎት አሰጣጡ ከአቀባበል ጀምሮ ያለው መስተንግዶ ቀደም ሲል ከነበረው አሠራር ፈጣን እና ቀልጣፋ መሆኑን ጠቁመው፣ በተሰጣቸው አገልግሎት እጅግ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

በተንቀሳቃሽ መሶብ አገልግሎት ለመጀመሪያ ጊዜ መገልገላቸውን የተናገሩት አቶ ዋበላ ሐጂከድር፤ አገልግሎቱን ባጠረ ጊዜ እና ቀልጣፋ በሆነ መልኩ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።


 

 መንግሥት ለህዝብ ፈጣን አገልግሎት በመስጠቱ  ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በኢፌዴሪ መሶብ አገልግሎት ተንቀሳቃሽ  አገልግሎት የኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ካውንተር ባለሙያ ደርቤ ፋንታሁን፤ ቀደም ሲል ተገልጋዮች አገልግሎት ለማግኘት ወደ ተቋሙ በአካል ለመሄድ ይገደዱ እንደነበር ያስታውሳሉ።


 

አሁን በተዘረጋው ተንቀሳቃሽ መሶብ አገልግሎት በሰለጠኑ ባለሙያዎች በመታገዝ በርካታ ተቋማትን ባቀናጀ መልኩ አገልግሎቶችን በአንድ ቦታ እየሰጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

በኢፌዴሪ መሶብ አገልግሎት ተንቀሳቃሽ  አገልግሎት የሁሉ አገልግሎት ባለሙያ ሃና ተፈራ፤ እስካሁን ድረስ ወደ ሁሉም ክፍለ ከተሞች በመንቀሳቀስ አገልግሎቶችን ተደራሽ በማድረግ የተገልጋዮችን እርካታ እያረጋገጥን እንገኛለን ብለዋል።

የኢፌዴሪ መሶብ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዮናስ ዓለማየሁ እንደገለጹት፤ ቀደም ሲል ተበታትነው የነበሩ የመንግሥት አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ በማድረግ በአንድ ማዕከል ተደራሽ ለማድረግ የተጀመረው የመሶብ አገልግሎት ከፍተኛ ሀገራዊ ውጤት እያስመዘገበ ነው።


 

ይህም በመሶብ ማዕከላት በአካል በመሄድ መገልገል ለማይችሉ ዜጎች መኖሪያ አካባቢያቸው ድረስ ሄዶ ማገልገል የሚቻልበት ሥርዓት መዘርጋቱን ተናግረዋል።

ይህ አሠራር በአካል መገኘት ለማይችሉ ዜጎች ትልቅ ዕድል የፈጠረ በመሆኑ በቀጣይም አገልግሎቱን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሠራ አቶ ዮናስ ዓለማየሁ አረጋግጠዋል።

 

 


 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም