ቀጥታ፡

የአካል ጉዳተኞችን የልማት ተሳትፎ ለማሳደግ የሚደረጉ እገዛዎች ተጠቃሚነትን እያሳደጉ ነው

ሰመራ፤ መስከረም 8/2019 (ኢዜአ):- የአካል ጉዳተኞችን የልማት ተሳትፎ ለማሳደግ የሚደረጉ እገዛዎች ተጠቃሚነትን እያሳደጉ መሆናቸውን የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ገለፀ።

ኢትዮ ቴሌኮም በአፋር ክልል በሠመራ ከተማ የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን  የትምህርት ተሳትፎ ለማሳደግ ያለመ የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።

በርክክብ ስነ ሰርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ተወካይ አቶ ብርሃኑ ንጉሴ የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን የትምህርት ተሳትፎ ለማሳደግ የሁሉንም አካላት የነቃ ተሳትፎን ይጠይቃል።


 

በዚህ ረገድ ኢትዮ ቴሌኮም ያደረገው ድጋፍ የተማሪዎቹን ውጤታማነት ከማሳደግ ባለፈ ማህበራዊ ኀላፊነትን መወጣት ያስቻለ መሆኑን ተናግረዋል ።

የአካል ጉዳተኞችን የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚደረጉ እገዛዎች  አብሮነትን የሚያጠናክሩ ተደማሪ አቅም መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ፌዴሬሽኑ በትምህርት ዘመኑ የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን የትምህርት አቀባበል ለማሳደግ በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች ስር ለሚገኙ 10 ሺህ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች  የግብአት  ድጋፍ ማድረጉን  ገልፀዋል።


 

የአፋር ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኀላፊ  ነስሮ ኡዳ እንዳሉት፤ በክልሉ ልዩ ትኩረት የሚያሻቸው የማህበረሰብ ክፍሎችን የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ በቅንጅት እየተሰራ ነው። 

ልዩ ድጋፍ የሚሹ ተማሪዎችን ማህበራዊ ጫና ለማቃለል ለ2019 የትምህርት ዘመን  የትምህርት ቁሳቁስ በማቅረብ ተወዳዳሪነታቸውን ለማሳደግ መሰራቱን አንስተዋል።

ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የተደረገው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማህበራዊ ሀላፊነትን በመወጣት ብቁ ዜጋን ለማፍራት ተደማሪ አቅም እንደሚሆን ጠቁመዋል።


 

በኢትዮ ቴሌኮም የሰሜን ምስራቅ ምስራቅ ሪጅን ተወካይና የገመድ አልባና መሰረተ ልማት አገልግሎት ዘርፍ ኀላፊ አቶ ሱራፌል አረፈ ሸዋ፤ በበኩላቸው ኢትዮ ቴሌኮም ከመደበኛ ስራው በተጓዳኝ ማህበራዊ ሀላፊነቱን በመወጣት አጋርነቱን እያሳየ ነው ብለዋል።

የተደረገላቸው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ እንደሚያግዛቸው  የተናገሩት ደግሞ ተማሪ ኡስማን ሁሴንና ዓሊ መሐመድ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም