ቀጥታ፡

የጅማ ዩኒቨርሲቲ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ማዕከል ተማሪዎች በፈጠራ ስራዎች ላይ በስፋት እንዲሳተፉ እያገዘ ነው

ጅማ ፤ መስከረም 8/2019 (ኢዜአ):-የጅማ ዩኒቨርሲቲ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ማዕከል ተማሪዎች በዘርፉ ያላቸውን እውቀትና ግንዛቤ በማሳደግ በምርምርና በፈጠራ ስራዎች ላይ በስፋት እንዲሳተፉ እያገዘ  መሆኑን ገለጸ።

በአሁኑ ወቅት የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) በዓለም አቀፍ ደረጃ በቴክኖሎጂ፣ በኢኮኖሚ፣ በጤና፣ በእርሻ እና በትምህርት ዘርፎች ፈጣን ለውጥ እያመጣ የሚገኝ ቁልፍ የፈጠራ መሳሪያ ነው። 

በኢትዮጵያም ሀገራዊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እቅድን ለማሳካት እና  የኢንዱስትሪ አብዮት ተሳትፎን ለማሳደግ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ አቅም ያላቸውን ወጣቶች ማፍራት ወሳኝ ጉዳይ ሆኗል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲም ይህንን ዓለም አቀፋዊ የቴክኖሎጂ ሽግግርና ሀገራዊ ፍላጎት ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ የተማሪዎችን የፈጠራና የምርምር አቅም ለማጎልበት የሰው ሰራሽ አስተውሎት ማዕከል አቋቁሞ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። 


 

ማዕከሉ ተማሪዎች የንድፈ ሐሳብ እውቀትን ከተግባራዊ ልምድ ጋር እንዲያናብቡ፣ በችግር ፈቺ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ላይ እንዲሰማሩ እና በዲጂታል ዘርፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማስቻል ያለመ ነው።

በዩኒቨርሲቲው የማዕከሉ ዳይሬክተር ኢንጂነር ጃርሚያ ባይሳ እንዳሉት፤ የዩኒቨርሲቲው የሰው ሰራሽ አስተውሎት ማዕከል ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ተማሪዎች በዘርፉ የሚያሳዩትን እውቀትና ግንዛቤ ለማጎልበት ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል።


 

ማዕከሉ ተማሪዎች በሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ የተመሰረቱ የፈጠራ ስራዎችንና ሶፍትዌሮችን እንዲያበለጽጉ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል ።

እንዲሁም ልዩ ልዩ እውቀትና ግንዛቤ ያላቸው ተማሪዎች በአንድ የስራ ቦታ በመሰባሰብ ልምድ የሚለዋወጡበት እድል ማመቻቸቱን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ተማሪዎች በማዕከሉ የስራ ላይ ልምምድ የሚያደርጉበትን እድል በመፍጠር፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የታገዙ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመስራት ተግባራዊ ልምድና እውቀት እንዲገበዩ እያደረገ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

በዓመት ሁለት ጊዜ ደግሞ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዙሪያ የሃካቶን ውድድር በማዘጋጀት፣ ተማሪዎች በፈጠራ እንዲወዳደሩና የልዩ ልዩ ሽልማቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ እድል እያመቻቸ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

የማዕከሉ እንቅስቃሴዎችም በዩኒቨርሲቲው ጊቢ ብቻ የተገደቡ አለመሆናቸውን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፣ ተማሪዎችና መምህራን በሰው ሰራሽ አስተውሎት የታገዙ ተጨባጭ የማህበረሰብ ችግሮችን የሚፈቱ የምርምርና የፈጠራ ስራዎች ላይ በስፋት እየተሳተፉ እንደሚገኝ ገልጸዋል።


 

ከተከናወኑ የፈጠራ ስራዎች መካከል በቡና ላይ የሚከሰቱ በሽታዎችን ቀድሞ ለመለየት፣ መፍትሄ ለመስጠት እና የቡና ደረጃን ለመወሰን የሚያገለግለው "ደቦ ቡና አፕ" ፈጠራን ለአብነት አንስተዋል።

እንዲሁም ባህላዊ ጨዋታዎችን በሮቦቲክስ እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት በማቀናጀት የሚያቀርብ ፕሮጀክት፣ የአፈርን ይዘት በመለየት ተስማሚ የምርት አይነት የሚያመላክተው "ኦሚሽቱ ጆይ አፕ" እና የእንስሳትን ጤና እና በሽታ ለመከታተል የተሰሩ ፈጠራዎች እንደሚገኙበትም አመልክተዋል።

በሰው ሰራሽ አስተውሎት የታገዙ እነዚህና ሌሎች ፕሮጀክቶች በተማሪዎችና መምህራን ንቁ ተሳትፎ የሚከናወኑ መሆናቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ስራዎቹ በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ሽልማቶችና እውቅናዎችን ማጎናጸፋቸውን ጠቁመዋል።

ማዕከሉ በቀጣይም ተማሪዎች፣ መምህራንና ተመራማሪዎች በዘርፉ የታገዙ ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችን እንዲያከናውኑና በርካታ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ የተመሰረቱ ጀማሪ ድርጅቶች (ስታርት አፕስ) እንዲቋቋሙ በትኩረት እንደሚሰራ ዳይሬክተሩ አመላክተዋል።


 

ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በዘርፉ የተመረቀችውና በተለያዩ የፈጠራ ስራዎች ላይ ስትሳተፍ የቆየችው ወጣት ኢክራም አልቃድር፣ በማዕከሉ የነበራት ቆይታ ከፍተኛ እውቀትና ልምድ እንድታካብት እንደረዳት ገልጻለች።

በአሁኑ ወቅትም በግል ተቋም ውስጥ በዘርፉ ተሰማርታ ውጤታማ ስራዎችን በማከናወን ላይ ትገኛለች።

ሌላኛው ወጣት አደም ሰይድ በማዕከሉ ያገኘውን እውቀትና ልምድ በመጠቀም 'ክሬቲቭ ሀብ' በተሰኘ ተቋም ውስጥ በመስራት ላይ ይገኛል።

በአሁኑ ወቅት በሶፍትዌር ማበልፀግ ስራዎች ላይ ተሰማርቶ እንደሚገኝ የገለጸው ወጣቱ፣ የጅማ ዩኒቨርሲቲ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ማዕከል ለስኬቱ ትልቅ መሰረታዊ እውቀት እንዳበረከተለት ጠቅሷል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም