ቀጥታ፡

የ"ጊፋታ" በዓል የአብሮነት እሴቶችን ለትውልድ ለማስተላለፍ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ይጠናከራሉ

ወላይታ ሶዶ ፤ መስከረም 8/2019 (ኢዜአ):-የ"ጊፋታ" በዓል የአብሮነት እሴቶችን ለትውልድ ለማስተላለፍ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የወላይታ ዞን አስተዳደር አስታወቀ፡፡

"የትውልድን ቅርስ እንጠብቅ፤ የጊፋታን ውርስ እናስቀጥል" በሚል መሪ ሐሳብ የሩጫ ውድድር በወላይታ ሶዶ ከተማ ተካሄዷል።


 

በወቅቱም የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ፣ የጊፋታ በዓል የአብሮነትና የአንድነት እሴቶችን ለትውልድ ለማስተላለፍ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡

ጊፋታ የኅብረ-ብሔራዊነትና የሰላም መገለጫ በመሆኑ በዓሉ አብሮነትን በማጠናከር የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በየዓመቱ የሚካሄዱ የጊፋታ ጨዋታዎች፣ የጊፋታ ጉዞና እና የጊፋታ ሩጫን በማጠናከር በዓሉ የፍቅርና የሰላም መሆኑን የማስተዋወቅ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

የወላይታ ሶዶ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ እታገኝ ኃይለማርያም በበኩላቸው፤ ጊፋታ በቂ ዝግጅት በማድረግ በጉጉት ጠብቀን የምናከብረው የሕዝብ በዓል ሆኗል ብለዋል።


 

በመሆኑም በወላይታ ሶዶ ከተማ በድምቀት ለማክበር በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልጸው በመሰል ሩጫ ላይ መሳተፍ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በጋራ አቅም ለማስቀጠል ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

የሩጫ ውድድሩ በዜጎች መካከል ኅብረ-ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ለአካባቢው ልማትና እድገት በጋራ ለመንቀሳቀስ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የወላይታ ዞን ባህልና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ስምኦን ስላሎ ናቸው፡፡


 

በዕለቱ በተካሄደ ውድድር በወንዶች ምድብ እስራኤል አባተ፣ በሴቶች ምድብ ደግሞ ምንትዋብ ወልዴ አንደኛ በመሆን አጠናቅቀዋል።


 

በወንዶች ምድብ ውድድር አንደኛ የወጣው እስራኤል አባተ በጊፋታ ሩጫ በተከታታይ ለሁለተኛ ጊዜ በማሸነፉ ደስተኛ መሆኑን ተናግሯል።

አሸናፊዎቹ በሰጡት አስተያየት መሰል ውድድሮች በሕዝቦች መካከል ያለው ትስስር እንዲጠናከር ያደርጋሉ ብለዋል።


 

ጊፋታ የሕዝብ ሀብት በመሆኑ አቅማቸውን በማሳደግ የተሻለ በመሥራት ሀገርን ወክለው የኢትዮጵያን ባንዲራ በዓለም አደባባይ ለማውለብለብ በርትተው እንደሚሠሩም ተናግረዋል።

በውድድሩ በሁለቱም ምድቦች ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ለወጡ አትሌቶች የገንዘብና የሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም