በምስራቅ ቦረና ዞን ከ57 ሺህ በላይ ዜጎች የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ተጠቃሚ ሆነዋል - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ቦረና ዞን ከ57 ሺህ በላይ ዜጎች የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ተጠቃሚ ሆነዋል
ነገሌ ቦረና ፤ መስከረም 8/2019 (ኢዜአ):-በምስራቅ ቦረና ዞን ከ57 ሺህ በላይ ዜጎች የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ተጠቃሚ መሆናቸውን የዞኑ ጤና ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡
የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በህመም ጊዜ ለከፍተኛ የህክምና ወጪ እንዳይጋለጡና ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት በቅናሽ እንዲያገኙ ታስቦ የተዘረጋ ስርዓት ነው።
በተለይም በገጠሩ የሀገሪቱ ክፍልና መደበኛ ባልሆነው የኢኮኖሚ ዘርፍ ለተሰማሩ ዜጎች የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን በማረጋገጥ በኩል ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
በምስራቅ ቦረና ዞንም የህብረተሰቡን የግንዛቤ ደረጃ በማሳደግና የአባልነት ክፍያን በማቀላጠፍ የመድህን ሽፋኑን ወደ ሁሉም ወረዳዎችና ገጠር ቀበሌዎች ለማስፋፋት ሲሰራ ቆይቷል።
በዞኑ ጤና ጽህፈት ቤት የሀብት ማመንጨትና የህብረተሰብ ተሳትፎ አስተባባሪ አቶ ነጋሽ ቀነኒ፤ ዘንድሮ ወደ 102 ሺህ ለሚጠጋ አባወራ የጤና መድህን ሽፋን ለመስጠት ታስቦ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል፡፡
እስካሁን በተደረጉት እንቅስቃሴዎች ነገሌ ቦረና ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ በሁሉም የዞኑ ወረዳዎች 57 ሺህ 453 ዜጎች የጤና መድህን ሽፋኑ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ከነዚህ ውስጥ ከ7 ሺህ 450 በላይ የሚሆኑት የጤና መድህን አገልግሎት ሽፋን ያገኙ አዳዲስ አባላት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
እንዲሁም 50 ሺህ 100 አባወራዎች የጤና መድህን ሽፋኑ ተጠቃሚ የነበሩና የአገልግሎቱን መታወቂያ ያደሱ ነባር አባላት መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚተዳደሩ ለ12 ሺህ 54 አባወራዎች የጤና መድህን ሽፋን ቅድመ ክፍያ በወረዳና በከተማ አስተዳደር መሸፈኑን ጠቁመዋል፡፡
በዞኑ በሚገኙ 3 ሆስፒታሎችና በ28 ጤና ጣቢያዎች አመቱን ሙሉ ነጻ የህክምና አገልግሎት አሰጣጡ ተደራሽ እንደሆነም አስተባባሪው አረጋግጠዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ከሀዋሳ፣ ሜጋ፣ ሞያሌ፣ ያቤሎ፣ ደሎ መና፣ ጎባ ስፔሻልይዝድ እና ከጎባ ሪፈራል ሆስፒታሎች ጋር ስምምነት ተፈራርመው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ነገሌ ቦረና ከተማን ጨምሮ ሁሉም ወረዳዎች 13 አዳዲስ የማህበረሰብ አቀፍ መድሃኒት ቤቶች መክፈታቸውንም ገልጸዋል፡፡
በዞኑ ባለፈው አመት የጤና መድህን ሽፋን ያገኙ 370 ሺህ 273 ዜጎች ነጻ የህክምና አገልግሎት ማግኘታቸውንም አስታውሰዋል፡፡
ከአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች መካከል የነገሌ ቦረና ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አበበች ወርቁ፤ አመታዊ ቅድመ ክፍያ በመፈጸም ሙሉውን ዓመት ከሶስት ቤተሰብ አባሎቻቸው ጋር የጤና መድህን ሽፋን ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡
የዚሁ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ታሪኳ ደምሴ የጤና መድህን አባል በመሆናቸው ሳይቸገሩ ነጻ የህክምና ክትትል ለማድረግ እንደቻሉ ተናግረዋል።
የጤና መድህን ሽፋን ሳይታሰብ ድንገኛ ህመም ሲያጋጥም ታክሞ ለመዳን እለታዊ ወጪን የማይጠይቅ በመሆኑ ዘርፈ ብዙ ጥቅም አለው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የጤና መድህን አገልግሎት የምርመራ፣ የመድሃኒትና ሌሎች የህክምና ወጪ ስለሚሸፈን ኢኮኖሚያዊ ችግርን የማቃለያ መሳሪያ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡