ቀጥታ፡

ወደ 300 የሚጠጉ የህገወጡ ህወሃት ታጣቂዎች እጃቸውን ሰጡ

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 8/2019 (ኢዜአ) ፦ የህገ ወጡን ህወሃት የጦርነት ዝግጅት በመቃወም ወደ 300 የሚጠጉ ታጣቂዎቹ በተከዜ በኩል ለሚገኘው ለሰሜን ምዕራብ ዕዝ እጃቸውን ሰጥተዋል።

በምዕራብ ግንባር ተከዜ አቅጣጫ ልዩ ቦታው በተከዜ ድልድይ ግራና ቀኝ አቅጣጫ ለዕዙ ሠራዊት እጅ የሠጡ የህወሃት ታጣቂዎች የኢትዮጵያ ጠላት ሆኖ የትግራይን ህዝብ ሲጨፈጭፍ ከነበረው ሻዕቢያ ጋር ፅምዶ በሚል የፈጠሩት ጥምረት ለትግራይ ህዝብ የማይጠቅም መሆኑን ታጣቂዎቹ ገልጸዋል።

ይሄንን በመገንዘብም በቀጣናው ከሚገኘው መከላከያ ሠራዊት ጋር ቀደም ብለው በመሠረቱት ግንኙነት በመነጋገር እና መንገድ በማመቻቸት እጅ መሥጠት እንደቻሉ ተናግረዋል።


 

የትግራይ ህዝብ ጥያቄ የሚፈታው በጠብመንጃ እንዳልሆነ በመረዳት እጃቸውን የሰጡት ታጣቂዎቹ ከ280 በላይ የነፍሰ ወከፍና የቡድን መሣሪያዎች፣ በርካታ የተለያዩ ዓይነት ተተኳሾች፣ የጦር ሜዳ መነፅርና ልዩ ልዩ ዶክመንቶች ይዘው ገብተዋል።

ራሳቸውን ከተጠያቂነት ለማዳን ሠላማዊውን የትግራይ ህዝብ ወጣት በማፈስ ወደ ጦርነት ለመማገድ የሚሠሩ ዘራፊ እና ወርቅ አውጪ የህገወጡ ህወሃት አመራሮችን ፍላጎት እንደሚቃወሙም ገልጸዋል።

እጅ ከሰጡ ታጣቂዎች መካከል ከክፍለጦር አዛዥ ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ የሻለቃና የሻምበል አመራሮች ይገኙበታል ያለው ዕዙ ይህ የሚያመላክተው ታጣቂው ሃይል ሳይፈልግ በህወሃት ሥርዓት አገዛዝ አስገዳጅነት የሚዋጋ ስለመሆኑም ገልጿል።


 

ህወሃት ከጦርነት አዙሪት የመውጣት ፍላጎት የሌለው ፅምዶ በሚል አካሔድ ህዝቡን አሁንም ወደ ከፋ ችግር ውስጥ ለመክተት የሚጥር፤ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ለሠላም የማይመች፤ የቀረበለትን የሠላም አማራጭ የማይቀበል በትግራይ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያጣ ስለመሆኑም እጅ የሠጡ ታጣቂዎች ተናግረዋል።

አሁን ላይ የህወሃትን የአገዛዝ ሥርዓት በመጥላትና ሠላምን በመምረጥ እጅ ለመስጠት የሚጠባበቁ በርካታ የትግራይ ወጣቶች አሉ ያሉት ታጣቂዎቹ የትግራይን ህዝብ ከኢትዮጵያ ህዝብ ለመነጠልና ሠላም ለማሳጣት ህወሃት ወጣቱን እያስገደደ ሳይፈልግ ለጦርነት እያዘጋጀ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ተገዶ የገባው የትግራይ ወጣትም ይህን አውቆ እና ተረድቶ ጊዜና ሁኔታው ሲመቻችለት እጅ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ከመከላከያ ሚዲያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም