ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ማንሠራራት እና የመግባባት ዴሞክራሲ ልዕልና

ኢትዮጵያ ከተለመደው የፖለቲካ የመገፋፋት አካሄድ ወጥታ፣ ሁሉንም ዜጎች የሚያካትትና በጋራ መግባባት ላይ የተመሠረተ አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች።
 
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉዞ ሀገሪቱን በፅኑ መሠረት ላይ ለማቆም እና ብሔራዊ መግባባትን በዘላቂነት ለማምጣት የሚያስችል ስኬታማ ተግባር ነው።
 
የምክክሩ ሂደት በሃሳብ መግባባትን ማዕከል ያደረገ በመሆኑ፣ የፖለቲካ ስጋቶችን እና አለመተማመኖችን በእጅጉ ይቀንሳል።
 
የመግባባት ዴሞክራሲ ዋነኛ መርህ ውሳኔዎች በአብላጫ ድምፅ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ወገኖች ስምምነት ላይ እንዲመሰረቱ ማድረግ ነው።
 
በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሂደትም መግባባት ላይ የተደረሰባቸው አጀንዳዎች ከጥቂቶች ፍላጎት የፀዳ፣ የብዙሃኑ ድምጽና ሀሳብ ጎልቶ የወጣበት ነው።
 
ምክክሩ ከተለመደው የፖለቲካ አካሄድ ተላቆ በምክንያት ላይ የተመሰረተ የውይይትና የመደማመጥ ባህል የዳበረበት ሲሆን ይህ መንገድ ለዘመናት የቆዩ አለመግባባቶችን በሰከነ መንፈስ ለማስተናገድ አስችሏል።
 
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክር ኮሚሽን ከአስፈጻሚው አካል ጣልቃ ገብነት ነፃ በመሆን በቀጥታ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪ እንዲሆን መደረጉ፣ ተቀባይነትና ተአማኒነት እንዲያገኝ አስችሏል።
 
በተለመደው የፖለቲካ ሥርዓት አጀንዳዎች የሚቀረጹት በጥቂት ልሂቃን ቢሆንም፣ በዚህ ምክክር ግን አጀንዳዎች ከታችኛው የህብረተሰብ ክፍል (ከወረዳ ደረጃ) በተሰበሰቡ ግብዓቶች ላይ ተመስርተው እንዲዘጋጁ መደረጉ ህዝቡ የሂደቱ ባለቤት እንዲሆን አድርጓል።
 
የተለያዩ ማህበረሰቦች ድምፃቸው እኩል ክብደት ኖሮት ውሳኔዎች ላይ እንዲሳተፉ መደረጉ የምክክሩ አንዱ ስኬት እና የኢትዮጵያ የማንሰራራት ጉዞ ማሳያ ነው ማለት ይቻላል።
 
ከዚህ በፊት የነበረው የአሸናፊና ተሸናፊ ፖለቲካ አካሄድን ያስቀረው ሀገራዊ ምክክሩ በጠረጴዛ ዙሪያ በመቀመጥ ሁሉንም አካላት አሸናፊ የሚያደርግና የጋራ መፍትሔ ማፈላለጊያ መድረክ ሆኗል።
 
የምክክር ጉባኤው መጠናቀቅ የሂደቱ ማብቂያ ሳይሆን ወደ ተግባራዊ ምዕራፍ መሸጋገሪያ ነው።
 
ኮሚሽኑ ያሰባሰባቸውን ከ400 በላይ ምክረ-ሀሳቦች ለተቋማት በማቅረብ እና የተገኙት ስምምነቶች መሬት ላይ መውረዳቸውን የሚከታተል የቁጥጥር ሥርዓት እያዘጋጀ ይገኛል።
 
በምክክሩ ላይ የታየው ሰፊና ሁለንተናዊ የህዝብ ተሳትፎ ኢትዮጵያን በጠንካራ መሰረት ላይ በመገንባት፣ ብሔራዊ መግባባትን እውን ለማድረግ እና የጋራ መጻኢ ዕድልን ለመቅረጽ የሚያስችል የዚህ ዘመን የመግባባት ዴሞክራሲ ተጨባጭ ማሳያ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም