ግብፅ የዓባይን ጉዳይ ለውስጥ ፖለቲካ ችግሮቿ መሸፈኛ ለማድረግ እየሞከረች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ግብፅ የዓባይን ጉዳይ ለውስጥ ፖለቲካ ችግሮቿ መሸፈኛ ለማድረግ እየሞከረች ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 7/2019 (ኢዜአ)፦ ግብፅ በዓባይ ወንዝ ላይ የምታደርገው የፖለቲካ ዘመቻ የራሷን ውስጣዊ ችግሮች ለመሸፈን የምትጠቀምበት ስልት መሆኑን የስትራቴጂክ ጥናትና የትስስር ኢኒሸቲቭ ማዕከል ከፍተኛ ተመራማሪ አብዱሻኩር አብዱሰመድ ገለጹ።
የግብፅ መንግስት አባይን ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋሉ እና የተፋሰሱን ሀገራት በጠላትነት ፈርጆ ማሳየቱ በግብጻውያን ዘንድ ኢትዮጵያ ላይ የተሳሳተ ጥላቻ እንዲኖራቸው ለማድረግ መሆኑን ከፍተኛ ተመራማሪው ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።
የሚዲያ ዘመቻ እና የተሳሳተ ትርክት ከውጤታማነቱ ይልቅ የግብፅን ህዝብ ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑን አመልክተዋል።
የግብፅ መንግስት ዓባይ ብቸኛው የውሃ ምንጭ እንደሆነ በማስመሰል ለማሳመን ረዥም ረቀት መጓዟን ጠቅሰዋል።
ይህ የተሳሳተ አመለካከት አንዳንድ ግብፃዊያን በሌሎች ሀገራት የሚደረጉ የልማት ስራዎች የግብፅን የውሃ ድርሻ የሚነጥቁ አድርጎ እንዲመለከቱ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።
የዚህ ሁሉ ዘመቻ ዋና ዓላማ በግብፅ ውስጥ የሚስተዋሉ ፖለቲካዊ እና ማሕበራዊ ቀውሶች ትኩረት እንዳያገኙ መሸፈኛ ማድረግ መሆኑን ነው ተመራማሪው ያስረዱት።
አክለውም፣ ትውልዱ ይህንን የተሳሳተ ትርክት እንደ ፍጹም እውነት እንዲቀበለው ግብፅ የምትሰራው ስራ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አንስተዋል።
ግብፅ ሜዲትራኒያን እና ቀይ ባህርን ጨምሮ በርካታ የባህር ዳርቻዎች እና የከርሰ ምድር የውሃ ሀብቶች እንዳሏት ተመራማሪው ጠቁመዋል።
ሆኖም በዓባይ ላይ ብቻዋን የመወሰን መብት እንዲኖራት ትፈልጋለች፣ ይህ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ጉዳይ ነው ብለዋል።
የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት (CFA) ሁሉም ሀገራት ፍትሃዊ የመጠቀም መብት እንዳላቸው በግልጽ እንደሚያስቀምጥም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን ጨምሮ ለሃይድሮ ኤሌክትሪክ ሃይል ለመጠቀም የማንንም ፈቃድ እንደማትጠይቅ እና ይህ ተፈጥሯዊ መብቷ መሆኑ የአደባባይ ሀቅ ነው።
ሀገሪቱ ንጹህ፣ ታዳሽ እና ደህንነቱ የተጠበቀ የኤሌክትሪክ ሃይል በማመንጨት ሚናዋን በሚገባ እየተወጣች ትገኛለች።
ኢትዮጵያ ከጅማሮው አንስቶ ከታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ጋር በትብብር ለመስራት ተደጋጋሚ ጊዜ ጥሪ አድርጋለች።
ይሁን እንጂ ግብፅ የመረጠችው አካሄድ ለጋራ ዕድገት እና ለፍትሃዊ ተጠቃሚነት ከሚያስፈልገው የትብብር አማራጭ ጋር ፍጹም የተቃረነ መሆኑን ከፍተኛ ተመራማሪው አንስተዋል።
ጊዜያዊ የፖለቲካ ቅስቀሳዎች ዕድሜያቸው አጭር ነው ያሉት ተመራማሪው በህዝቦች ውስጥ የሚፈጥረው የተሳሳተ ግንዛቤ በጊዜ ሂደት እንደሚቀረፍም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።