የዓባይ ወንዝና የቀይ ባሕር ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ ጉዳይ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የማስከበር ማዕከላዊ አጀንዳዎች ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
የዓባይ ወንዝና የቀይ ባሕር ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ ጉዳይ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የማስከበር ማዕከላዊ አጀንዳዎች ናቸው
አዲስ አበባ ፤ መስከረም 7/2019 (ኢዜአ)፦የዓባይ ወንዝ ፍትሐዊ የውሃ ሀብት ተጠቃሚነትና የባሕር በር ባለቤትነትን የማረጋገጥ ጉዳይ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የማስከበር ማዕከላዊ ስትራቴጂክ አጀንዳዎች መሆናቸውን ምሁራን ገለጹ።
የአዲስ አበባ አመራር አካዳሚ የዓባይ ወንዝና የባሕር በር ጉዳዮችን በተመለከተ የፓናል ውይይት አካሂዷል።
የማኅበራዊ ሳይንስ ምሁሩ ብርሃኑ ሌንጂሶ (ዶ/ር) በፓናሉ ላይ እንዳሉት፣ የዓባይና የባሕር በር ጉዳዮች በጂኦፖለቲካዊና በልማታዊ ትስስራቸው ተነጣጥለው ሊታዩ አይገባም።
የዓባይ ወንዝ ጉዳይ የልማት፣ የኢኮኖሚና የቀጣናዊ ትብብር ማዕከል በመሆኑ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ አቀራረብ ሊከተል እንደሚገባ አመልክተዋል።
ሁለቱን ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች በተቀናጀ የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይና የልማት ስትራቴጂ መሠረት መምራት እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።
በዚህም የዓባይ ወንዝ ፍትሐዊ የውሃ ሀብት ተጠቃሚነትና የባሕር በር ባለቤትነትን የማረጋገጥ ጉዳይ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የማስከበር ማዕከላዊ ስትራቴጂክ አጀንዳዎች መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
የአዲስ አበባ አመራር አካዳሚ መሪ ተመራማሪ አቶ ሰለሞን ተፈራ በበኩላቸው፣ የባሕር በርና የዓባይ ጉዳዮች ተነጣጥለው ሳይሆን በአንድ ሀገራዊ ማዕቀፍ ውስጥ ተቀናጅተው ሊታዩ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ጉዳዮቹ በምሁራን ጥናትና በጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ሊመሩ እንደሚገባም ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝምና ገቨርናንስ መምህርና ተመራማሪ ተስፋዬ ጂማ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የባሕር በር ጉዳይ ከሉዓላዊነት፣ ከኢኮኖሚ ዕድገትና ቀጣናዊ ሰላም የተቆራኘ የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ ነው ብለዋል።
የሀገር ህልውናን፣ ደህንነትንና የዜጎችን ማኅበራዊ ልማት ከሚያሳድጉ ጉዳዮች አኳያ፣ የባሕር በርና የዓባይ ወንዝ ጉዳዮች በአንድ ማዕቀፍ ውስጥ ሊታዩ እንደሚገባ አንስተዋል።
ምሁራን በጥናትና ምርምር የተደገፈ የፖሊሲ ግብዓት በማቅረብ፣ እንዲሁም የሕዝብ ግንዛቤን በማሳደግ፣ ሀገራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ በሚደረገው ሂደት አዎንታዊ ሚና ማበርከት እንደሚችሉም ተናግረዋል።