የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት የዚህ ትውልድ አደራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት የዚህ ትውልድ አደራ ነው
ቀይ ባሕር ለኢትዮጵያ የውሃ አካሏና በሯ ብቻ አልነበረም፤ የሺህ ዘመናት የንግድ፣ የሥልጣኔ፣ የሃይማኖትና የባህል መገለጫ፤ ከዓለም ጋር ያላትን መስተጋብር ማሳለጫ መስመር ጭምር እንጂ።
የአክሱም ሥልጣኔ በቀይ ባሕር የጠረፍ ከተማዋ በኩል የከተመው የአዱሊስ ወደብ ላይ መልህቁን በመጣል ከዓረብ ልሳነ ምድር እስከ ሜዲትራኒያን፣ ከሕንድ ውቅያኖስ እስከ የአፍሪካ የባሕር ጠረፎች ድረስ የነበረው ሁለንተናዊ ትስስር የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነትና የንግድ ማዕከልነት ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ገናና የታሪክ አስረጂ ነው።
ኢትዮጵያ ምፅዋና አሰብ ወደቦቿን በግፍ ተነጥቃ ከቀይ ባህር ጂኦ ፖለቲካ ከተገለለች የጉልማሳ ዕድሜ አስቆጠረች፤ የቀጣናው የሥልጣኔ ፈር ቀዳጅ፣ የንግድ መስመር፣ የዲፕሎማሲ ማዕከል የነበረች ሀገር አምጣ በወለደቻቸው ልጆቿ ጭምር ደባ ተሰራባት ።
ለዚህም ነው ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ጋር የነበራት ጥብቅ ቁርኝት የዘመኑ የፖለቲካ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን ከጥንታዊ የንግድና የሥልጣኔ ታሪኳ ጋር የተሳሰረ የትውልድ የህልውና ጉዳይ የሚሆነው።
ግብጽ እና ሌሎች ታሪካዊ ጠላቶች የሀገር ውስጥ ባንዳዎችን በማስተባበር በፈጸሙት ደባ ኤርትራን ከኢትዮጵያ በመገንጠል የሺህ ዘመናት ገናና የሥልጣኔ ልዕልናዋን የሚያሳጣ ክህደት ፈጽመዋል።
ይኸውም ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብና ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበች ያለችውን የቀጣናው ሀያል ሀገር የሎጂስቲክስ እንቅስቃሴ በማስተጓጎል በገቢና ወጪ ንግድ እና በኢንቨስትመንት ፍሰት ላይ ዕንቅፋት ደቅኗል።
የዓለም ባንክ መረጃ እንደሚያመለክተው ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ የገቢና ወጪ ንግድ እንቅስቃሴ በአዲስ አበባ - ጅቡቲ ኮሪደር ብቻ የተወሰነ ነው፤ ከዚህም ባሻገር ቀይ ባህር የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የሰላምና የሕልውና ጉዳይ እየሆነ መጥቷል።
ከቀይ ባሕር በቅርብ ርቀት የምትገኘው ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ሰፊ የሕዝብ ቁጥርን፣ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትን፣ የሰላምና የደኅንነት ስጋት እንዲሁም የሕልውና ጉዳይን ሁሉ ታሳቢ ያደረገ ነው።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ፍትሐዊና ምክንያታዊ ነው። ህልውናን ማረጋገጥ፣ ከሌሎች ሀገራት ጋር የጋራ ጥቅምን በማስጠበቅ የኢኮኖሚ፣ የሰላምና ደኅንነት ትብብርን ማጠናከርና የጋራ ብልጽግናን የማረጋገጥ ግብም አንግቧል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጎረቤት ሀገራትን በሀይልና በመሰረተ ልማት በማስተሳሰር ኢትዮጵያ በጋራ ለመልማትና ለማደግ ያላትን ፅኑ ፍላጎት ያሳያል።
ኢትዮጵያ የቀይ ባህር ጂኦ ፖለቲካ እስረኛ ሆና ያሳለፈቻቸው ዓመታት በዓባይ ዘመን ትውልድ ሊያከትም ይገባል፤ ጥያቄዋም በዓለም አቀፍ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ መድረክ ቅቡልነት እያገኘ እንዴት ይፈጸም ወደሚል ወሳኝ ምዕራፍ መሸጋገሩ ይሄን እውነት ያንጸባርቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያን የባሕር በር አይገባትም የሚል ሰው የተፈጥሮን ህግ የሳተ መሆኑን አስረድተዋል።
ቀይ ባሕርና ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ተነጣጥለው መኖር እንደማይችሉ፤ ይሄንንም አምኖ መቀበል እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ጽናትን፣ ፈጠራ፣ ትብብርና ዘላቂነትን መገንባት በሚል መሪ ሃሳብ በሕንድ ኒው ዴልሂ በተካሄደው 18ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤም የኢትዮጵያን የዕድገትና ብልፅግና ተስፋና መፃኢ ዕድል አብራርተዋል።
ለኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት ከምንም ነገር በላይ ቀዳሚውና ወሳኙ የኢኮኖሚ ጉዳይ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ብሔራዊ ጥቅሟንና የአፍሪካን ድምፅ ለማስተጋባት የጉዳዩን ወሳኝነት ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ በግልጽ ተናግረዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ (ዶ/ር) ቀደም ሲል ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያውያን በተፈጸመ የታሪክ ስህተት የትውልድን ዘላቂ ብሔራዊ ጥቅም አሳልፈን የምንሰጥ ሕዝቦች አይደለንም ብለዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አማካኝነት የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ በይፋ በቀረበ ማግስትም በሕዝብ ልብ ውስጥ ለጥቂት ዓመታት ተዳፍኖ የቆየው ቁጭት በአጭር ጊዜ ውስጥ ቅቡልነት ማግኘቱን ገልጸዋል።
በቀጣይም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ዙሪያ ልዩነት ሊኖረን አይገባም ያሉት ሚኒስትሩ፤ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ትብብርና አንድነት ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈትሂ ማህዲ (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ቀጣናዊ ትብብርና የጋራ ብልጽግናን ማዕከል ያደረገ ነው ብለዋል።
ጥያቄው ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ፣ መልክዓ ምድራዊና ሕጋዊ መሰረት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገትንና የሕዝብ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ንግድና ኢንቨስትመንትን የማሳለጥ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የባሕር ሕግ ስምምነትና ሕግጋትም ወደብ አልባ ሀገራት ወደ ባሕር የመድረስና የመጠቀም መብታቸውን የሚደግፍ ድንጋጌና ማዕቀፍ እንዳለው አስረድተዋል።
በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የአፍሪካ ቀንድና የውሃ ጂኦፖለቲካ ከፍተኛ ተመራማሪ ጋሻው አይፈራም (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ የታሪክ ስብራትን በማረም ኢትዮጵያን ከገናና ታሪክና ሥልጣኔዋ የማስታረቅ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን በማጠናከር የአፍሪካን ኢኮኖሚ ውህደት ለማሳለጥ በምታደርገው ጥረት የባሕር በር ባለቤትነት አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።
የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄው ዓለም አቀፍ ቅቡልነት እያገኘ መሆኑን በማንሳት፤ ሀገራት፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትና መገናኛ ብዙኅን የጉዳዩን አስፈላጊነት በቅጡ መገንዘባቸውን አብራርተዋል።