ቀጥታ፡

የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን በመቋቋም የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የቀጣናው ሀገራት ወሳኝ የትብብር ማዕከል መሆን አለበት 

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 7/2019 (ኢዜአ)፦የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን በመቋቋም የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የቀጣናው ሀገራት ወሳኝ የትብብር ማዕከል መሆን እንዳለበት የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ገለጹ።

ኢጋድ እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ከ2026 እስከ 2035 ለ10 ዓመታት የሚተገብረውን የቀጣናው የግብርና ምርትና የምግብ ሥርዓት ኢንቨስትመንት ዕቅድ እና የኢጋድ ቀጣና የግብርና ዘር ፖሊሲ የባለሙያዎች ግምገማ በማድረግ በሚኒስትሮች አጸድቋል።

የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት፤ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን ለመከላከልና ለመቋቋም በትብብር የምንቆምበት ወሳኝ ወቅት ላይ ነው ያለነው ብለዋል ።

ኢጋድ በቀጣናው ሀገራት የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ የማይበገር ኢኮኖሚ መገንባት ቀዳሚ መርሁ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የኢጋድ የግብርና ምርትና የምግብ ሥርዓት ኢንቨስትመንት የ10 ዓመት ዕቅድ በቀጣናው ቀጣይነት ያለውና አይበገሬ የምግብ ሥርዓት መገንባት ያስችላል ብለዋል።

የኢጋድ ቀጣናዊ የግብርና ዘር ፖሊሲም የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን የሚቋቋም ዘላቂ ኢኮኖሚ ማንበር እንደሚያስችል ገልጸዋል።

በአፍሪካ አህጉራዊ ሽግግር ለመፍጠር የኢጋድ ኢኒሼቲቮች ጉልህ አበርክቶ እንዳላቸው ጠቁመው፤ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን በመቋቋም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የቀጣናው ሀገራት በትብብር መሥራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ለዚህ ደግሞ የኢጋድ ቀጣና ሀገራት ሕዝባቸውን፣ ሀብታቸውንና እውቀትን በማስተባበር፣ የፋይናንስ አቅምን ማጠናከርና ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሚገባቸው ገልጸዋል።


 

የግብርና ሚኒስትር ከፍተኛ አማካሪ ጌታቸው ድሪባ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የኢጋድ ቀጣና ሀገራት በባህል፣ በታሪክና በኢኮኖሚ የተሳሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ በዓለም አቀፍ የሥርዓተ ምግብ መዋቅር ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ጠቅሰው፤ ለተግባራዊነቱ መረባረብ ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ሥርዓተ ምግብና የግብርና ዘር ፖሊሲ ዋና አጀንዳዋ ነው ያሉት ከፍተኛ አማካሪው፤ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችል የትኩረት ማዕከል መሆኑንም ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም