ቀጥታ፡

የጋምቤላ ክልል ከተሞችን ለኑሮና ለኢንቨስትመንት ምቹ ለማድረግ የተጀመሩ ጥረቶች ይጠናከራሉ

ጋምቤላ ፤ መስከረም 7/2019 (ኢዜአ)፦ የጋምቤላ ክልል ከተሞችን ለኑሮና ለኢንቨስትመንት ምቹ ለማድረግ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሉዋክ ሮን (ዶ/ር) ገለጹ።

‎የክልሉ የከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምና የአዲሱ በጀት ዓመት እቅድ ላይ ያዘጋጀውን የውይይት መድረክ ዛሬ  አካሄዷል።


 

‎የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጋትሉዋክ ሮን (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የክልሉ ከተሞችን ለኑሮና ለኢንቨስትመንት ምቹ ለማድረግ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ።

ከተሞችን ለነዋሪዎችና ለኢንቨስትመንት ምቹ ለማድረግ የመሠረተ ልማት ማስፋፋት ላይ የተጀመረው ጥረት እንደሚጠናከርም ገልጸዋል።

ለዚህም የኮሪደር ልማትን ጨምሮ የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የውስጥ ለውስጥ መንገድና ሌሎች የመሰረተ ልማት አውታሮችን ተደራሽ በማድረግ የህዝቡን የመሰረተ ልማት ጥያቄ ለመመለስ ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል።

‎ህብረተሰቡ ለከተሞች የመሰረተ ልማት ግንባታ፣ ጽዳትና ውበት ስራዎች መሳካትም እያደረገ ያለውን ሁለንተናዊ ተሳትፎና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አጠናክሮ እንዲያስቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።


 

በበጀት ዓመቱ የተያዙ ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው የጊዜ ሰሌዳ ተጠናቀው ለሕዝብ አገልግሎት እንዲበቁም የክትትልና ድጋፍ ስራዎች ይጠናከራሉ ብለዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በከተሞች የሚታዩ የመጠጥ ውሃ፣ የውስጥ ለውስጥ መንገድና የፍሳሽ ማስወገጃ መስመር ተግዳሮቶችን ለመፍታት በትኩረት መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በግምገማ መድረኩ ላይ ከክልል፣ ከዞን፣ ከወረዳዎችና ከከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም