የዲጂታል ፍርድ ቤት አሰራር ፍትሃዊና ግልጽ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ወሳኝ ምዕራፍ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዲጂታል ፍርድ ቤት አሰራር ፍትሃዊና ግልጽ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ወሳኝ ምዕራፍ ነው
ድሬደዋ፤ መስከረም 7/2019 (ኢዜአ)፦የዲጂታል ፍርድ ቤት አሰራር ፍትሃዊና ግልጽ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምህረት አስታወቁ።
በድሬደዋ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች ከወረቀት ንክኪ የፀዳ የዲጂታላይዜሽን አገልግሎት ማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት ዛሬ ተካሂዷል።
አገልግሎቱ በተጀመረበት ወቅት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምህረት፣ የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር እና ሌሎች የክልልና የፌዴራል መስሪያ ቤት አመራሮች ተገኝተዋል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምህረት በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የፍትህ ትራንስፎርሜሽን ትግበራው የፍትህ ስርዓቱን ተደራሽ፣ ግልፅና ውጤታማ በማድረግ የህዝብ እርካታን ለማረጋገጥ እያስቻለ ይገኛል።
የፍርድ ቤቶች አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ ማድረግ ተገልጋዮች ባሉበት ቦታ ሆነው ጉዳያቸውን የሚከታተሉበትን ስርዓት ለመዘርጋት እንዳስቻለም ነው የጠቀሱት።
በተለይ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውስጥ የተጀመረውን የስማርት ኮርት ስርዓት በመላው አገሪቱ በማስፋት ፈጣንና ግልፅ የፍትህ አገልግሎት በማስፈን የተገልጋዩን እርካታ ለማረጋገጥ ማስቻሉን ገልጸዋል።
የፍርድ ቤቶችን መረጃ አያያዝ ለማዘመን ተግባራዊ የተደረጉ የዲጂታል አገልግሎቶችም ፈጣንና ተደራሽ ፍትህን ለማስፋት እንዳስቻሉም ነው የገለጹት።
ዛሬ በድሬደዋ ተመርቆ ወደ አገልግሎት የገባው የዲጂታል አገልግሎት አሰራር በክልሎች የተጀመሩትን አበረታች ውጤቶች በላቀ ደረጃ ለማሳደግ ለተከናወኑት ተግባራት ማሳያ እንደሚሆንም አንስተዋል።
የተጀመሩ የዲጂታል አገልግሎቶች የፍትህ ስርዓቱን ግልፅነትና ተጠያቂነት ከማስፈን ባሻገር፣ ተገልጋዮች ካሉበት ስፍራ ሆነው መረጃዎችን ለማግኘት እያስቻሉ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በበኩላቸው፤ የፍርድ ቤቶችን አሰራር ዲጂታላይዝ ማድረግ ፍትህን በእኩልነት፣ በግልፅነት እና በቅልጥፍና ተደራሽ ለማድረግ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅትም ፍርድ ቤቶች ከወረቀት ንክኪ የፀዳ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት የተገልጋዩን እርካታ ለማረጋገጥ እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።
በድሬዳዋ በተካሔደው የፍርድ ቤቶች የዲጂታላይዜሽን ይፋዊ ጅማሮ እና ጉብኝት ላይ የድሬደዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አብዲ ሙክታር እና ከፍተኛ አመራሮች፣ የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ፕሬዝዳንቶች፣ አመራሮች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ሆነዋል።