በአማራ ክልል የፍትሕ አገልግሎትን ቀልጣፋ ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት ተመዝግቧል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የፍትሕ አገልግሎትን ቀልጣፋ ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት ተመዝግቧል
ጎንደር ፤ መስከረም 7/2019 (ኢዜአ)፦በአማራ ክልል የፍትሕ አገልግሎትን ተደራሽና ቀልጣፋ ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት መመዝገቡን የክልሉ ፍትሕ ቢሮ አስታወቀ።
በቢሮው የጎንደር ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ያለፈው በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ መድረክ ዛሬ በጎንደር ከተማ አካሂዷል።
የክልሉ ፍትሕ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ወንዳቸው ሰራው በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ ቢሮው የፍትሕ አገልግሎትን ተደራሽ፣ ቀልጣፋና ዲጂታላይዝ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል።
ባለፈው በጀት ዓመትም ባከናወናቸው ተግባራት ከ22 ሺህ በላይ የወንጀል መዝገቦችን በመመርመር 99 በመቶ የሚሆኑት የፍርድ ውሳኔ እንዲያገኙ ማድረጉን ገልጸዋል።
በዚህም በወንጀል የተገኘ ከ430 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሀብት ወደ መንግሥት ካዝና እንዲመለስ ተደርጓል ብለዋል።
እንዲሁም ልዩ የሕግ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው አቅመ ደካሞች፣ ሴቶችና ሕፃናት ከ520 ሚሊዮን ብር በላይ ሊያስወጡ የሚችሉ ጉዳዮችን ይዞ ነፃ የሕግ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ነው ያሉት።
ቢሮው የመንግሥትንና የሕዝብን ጥቅም በማስጠበቅ የአገልግሎት አሰጣጡን በቴክኖሎጂ ተደራሽና ቀልጣፋ ለማድረግ የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ፍትሕ መምሪያ ኃላፊ አቶ አለልኝ ደሳለኝ በበኩላቸው፣ በዞኑ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥና ወንጀልን በጋራ ለመከላከል እንዲቻል እየተሰራ ይገኛል።
በዚህም የመንግሥትንና የሕዝብን ጥቅም ማስከበር ያስቻሉ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
መምሪያው ከፖሊስ፣ ከፍርድ ቤትና ከማረሚያ ቤቶች ጋር ቅንጅታዊ አሠራርን በማጠናከር ባከናወናቸው ተግባራት በወንጀል የተሳተፉ 1 ሺህ 238 ግለሰቦችን ማስቀጣቱን ተናግረዋል።
በተጨማሪም በወንጀል ድርጊት የተገኘ ሀብትን ለማስመለስ በተደረገ ጥረት ከ79 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሀብትና ንብረት በማስመለስ ለመንግሥት ገቢ እንዲሆን ተደርጓል ነው ያሉት።
ባለፈው በጀት ዓመት በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር፣ በፍትኃ ብሔርና በሰነዶች ምዝገባ ከ28 ሺሕ ለሚበልጡ ሰዎች የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠቱን የገለጹት ደግሞ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ፍትሕ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ ጌታቸው ናቸው።
ወንጀልን አስቀድሞ ለመከላከልም በትምህርት ቤቶችና በማኅበረሰብ አደረጃጀቶች ከ36 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች የንቃተ-ሕግ ትምህርት መስጠት መቻሉን አብራርተዋል።
በመድረኩ የክልል፣ የዞንና የወረዳ የዘርፉ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የዓቃቤ-ሕግ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።