ቀጥታ፡

ጊፋታ እና ኮርማ ጪሻ

"ጊፋታና ኮርማ ጪሻ"

(በማስረሻ ሐብታሙ ከኢዜአ ወላይታ ሶዶ ቅርንጫፍ)

የወላይታ ዘመን መለወጫ "ጊፋታ" በዓል ሲደርስ ሜዳና ጋራው በአበቦች ይደምቃል። የአበቦቹ መዓዛ አካባቢውን ያውዳል። ሕዝቡም የወደፊቱን ብሩህ ተስፋ በዐይነ-ሕሊናው እያሰበ ዕለቱን በናፍቆት ይጠብቃል።

ከአበቦች መካከልም ከሁሉ ቀድሞ የሚፈካው "ኮርማ ጪሻ" ወይም "የጊፋታ አበባ" በሰፊው መስክ ላይ ሌላ ውበትና ድምቀት ይፈጥራል። ''ኮርማ ጪሻ'' በወላይታዎች ዘንድ የጊፋታ በዓል ዋዜማና የመምጫ ወቅት መጠቆሚያ ከሆኑት የተፈጥሮ ምልክቶች አንዱ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ''ኮርማ ጪሻ'' ከአደይ አበባ የሚለይ ሲሆን፤ ነጭ ቀለም እና ትናንሽ ቅጠሎች ያሉት የአበባ ዓይነት ነው።


 

በወላይታ ዘመን አቆጣጠር መሠረት "ኩሻ አጊና" ወይም ከነሐሴ ወር አጋማሽ ጀምሮ በጊፋታ ወር መባቻ ላይ በአካባቢው በስፋት በማበብ ለእይታ ድምቀት የሚሰጥና የወላይታ አዲስ ዓመት መቃረቡን የሚያበስር ድንቅ የተፈጥሮ ስጦታ ነው "ኮርማ ጪሻ" ወይም "የጊፋታ አበባ"።

በጉዳዩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የወላይታ ታሪክ ተመራማሪ አቶ አዳነ አይዛ እንደሚያስረዱት፤ ቀደምት የወላይታ ሥነ-ፈለግ አዋቂዎች ዘመንን ለመቁጠር ከፀሐይ፣ ጨረቃ እና ከዋክብት እንቅስቃሴ በተጨማሪ፣ የተፈጥሮ ለውጦችን ከመልክዓ-ምድሩ ውበትና ከተፈጥሯዊ ምልክቶች ጋር አጣምረው ይጠቀሙ እንደነበር አውስተው፤ ይህ ''ኮርማ ጪሻ'' ትልቁ ማረጋገጫ ስለመሆኑም ይገልጻሉ።


 

"ጊፋታ" ሲቃረብ የወላይታ ሕዝብ ለበዓሉ ሙሉ ዝግጅት የሚያደርግበት አያሌ የተፈጥሮ ምልክቶች እንዳሉት ተመራማሪው ይናገራሉ። ወላይታዎች የዝናብና የአየር ንብረት ለውጥን መሠረት በማድረግ ጊዜን የሚቆጥሩ ሲሆን፤ የክረምቱ ከባድ ዝናብና ጨለማ ወቅት አልፎ ሙሉ የፀሐይ ብርሃን መተካት ''ቦቃልሳ'' ማለትም ''ኦፊንታ'' (የፀደይ ወቅት) ሊጀምር ሲል ለጊፋታ በዓል ጥቂት ቀናት ብቻ መቅረቱን በማጥናት አንዱ ከአንዱ መረጃ መለዋወጥ ይጀምራሉ ብለዋል።

የወንዞች ሙላትና መጉደልም እንደ አንድ ምልክት የሚወሰድ ሲሆን፤ ለሦስት ወራት ምድርን አጨልሞ የነበረው ጭጋግና የጉም ወቅት አልፎ በክረምቱ ጎርፍ ሞልተው የነበሩ ወንዞች ጊፋታ ሲቃረብ እየጎደሉ ይመጣሉ።

ጨረቃም በአዲስ መልክ ለመውጣት በአሮጌው ዓመት በጨለማ ውስጥ ለቀናት ቆይታ ''ጤሩዋ'' ወይም መውጫ ጊዜዋ ሲደርስ በ''ግሩዋ'' (በሥነ-ፈለግ አዋቂዎች) ዓይን ከታየች፤ አዲስ ዓመት መቃረቡን በአዋጅ ሳይነገራቸው እንዲሁ በተፈጥሮ ምልክት ብቻ ዝግጅት ማድረግ ይጀምራሉ። ይህ ብቻ አይደለም፤ የጊፋታ መምጣትን ጠቋሚ የሆነው የነጭ ቢራቢሮ መንጋ የወላይታን ምድር በመውረር ከአንድ አቅጣጫ ወደ ሌላኛው አቅጣጫ መብረር ሲጀምርም ጊፋታ መቃረቡን አመልካች  መሆኑን አቶ አዳነ ይገልጻሉ።

በዚህ ወቅት ልጆች የቢራቢሮ መንጋ ለማደን ወደ መስክ ወጥተው የሚያደርጉት ጨዋታ የጊፋታ መምጫን ልዩ ያደርገዋል፤ የበዓሉ መቃረብ ደወል ተደርጎም ይወሰዳል። በዚህ ትይዩ ወቅት የሚያብበው ''ኮርማ ጪሻ'' የክረምቱ ጨለማና ያ ከባዱ ዝናብና ጉም አልፎ ወደ ፀደይ ብርሃን በሚሸጋገርበት ወቅት የፀሐይን መውጣት ተከትሎ የሚመጣ ጊዜ ወይም ''ቦቃልሳ'' የሚባለው ወቅት ሊገባ ሲል መሆኑንም የዘርፉ ሊቃውንት ይናገራሉ።

በወላይታ ባህል "ኮርማ ጪሻ" ሲያብብ ኅብረተሰቡ የጊፋታ በዓል ዝግጅቱን በይፋ የሚያጧጧፍበት ልዩ የተፈጥሮ ጥሪ ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑን ተናግረው፤ ሳይሸራረፍ ዘመናትን እየተሻገረ ይኸው ለዛሬው ትውልድ መድረሱን የገለጹት ደግሞ በወላይታ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የባህል፣ የታሪክና ቅርስ ተመራማሪ አቶ ግርማ ገነነ ናቸው።


 

"ኮርማ ጪሻ" በወላይታዎች ዘንድ ለጊፋታ በዓል "እንኳን አደረሰህ / አደረሳችሁ!" ተብሎ የሚበረከት የመልካም ምኞት መግለጫ የአበባ ስጦታ መሆኑንም አመልክተዋል።

''ኮርማ ጪሻ'' በወላይታ የዘመን አቆጣጠር እና ተፈጥሯዊ ቀመር ውስጥ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው ምስጢራዊ አበባ መሆኑን የገለጹት አቶ ግርማ፤ ወደ አዲስ ዘመን መሻገሪያ ምልክት፣ የተስፋ እንዲሁም ከጨለማ ወደ ብርሃን መሸጋገርን የሚያበስርና ለመንፈስ እርካታን የሚሰጥ ነው ብለዋል።

የወላይታ የዘመን አቆጣጠር ሥርዓት በጨረቃ እና በፀሐይ ዑደት ላይ የተመሠረተ ሆኖ በዓሉ የሚከበርበትን ትክክለኛ ቀን፤ "አዋቂዎች" ከሚያደርጉት ስሌት ጎን ለጎን፣ የተፈጥሮ ጸጋ የሆነው ኮርማ ጪሻ ወይም የጊፋታ አበባ ፍንትው አድርጎ ያሳያል። አበባው የወቅቱን መለወጥና የአዲሱን ዓመት መባቻ በተፈጥሯዊ ቋንቋ የሚነግር ነው።

የዚህን አበባ ምስጢር ታላቅነት የሚያብራሩት ከሀገር ሽማግሌዎች አንዱ የሆኑት አቶ ኢያሱ ጋጃቦ በበኩላቸው፤ ይህ አበባ ለ"ጊፋታ" ወይም ለአዲስ ዘመን በዓል መግቢያ አንድ ወር ጊዜ ብቻ ሲቀረው የሚበቅልና ቀናት ሲቀሩት የሚያብብ ድንቅ የተፈጥሮ ፀጋ መሆኑን ይናገራሉ።

ኮርማ ጪሻን ከጊፋታ በዓል መምጫ ወቅት ውጭ በዓመት ውስጥ ፈልጎ ማግኘት እንደማይቻል ገልጸው፤ ይህንን ተፈጥሮ በመተርጎም ረገድ የቀደምት አባቶች አእምሯዊ ጥበብ ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል።

''ኮርማ ጪሻ'' ወይም የጊፋታ አበባ ከጊፋታ በዓል ማግስት ባለው ማክሰኞ ዕለት ወደ አማች ቤት ወይም ወደ አበልጅ ቤት "ዮዮ ጊፋታ" በማለት ይዞ በመሄድ ለአባዎራው ይሰጣል።

በዚህ ጊዜ አባወራው "ዮዮ ዮዮ" በማለት ተቀብሎ ከምሰሶ ጋር አስሮ ያስቀምጣል። ይህም የቤቱ መሶብ፣ በረከትና አዲሱ ዘመን እንደ ምሰሶው ጸንቶ እንዲኖር የሚደረግበት የአዲሱ ዓመት መቀበያ ምልክትና ምርቃት ነው፡፡

በዚህም ወቅት አባዎራው ''ጊፋታይ እንተና ቆዶፖ፤ እንቴ ጊፋታ ቆዲቴ'' ወይም "ዘመን እናንተን አይቁጠራችሁ፤ እናንተ ዘመናትን እየቆጠራችሁ ኑሩ" በማለት ይመርቃል።

"ኮርማ ጪሻ" የወላይታ ነባር የሥነ-ፈለግ እውቀት የሚገለጥበት ተፈጥሯዊ እውቀት መሆኑንም ተናግረዋል።

በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የወላይታ የዘመን መለወጫ በዓል "ጊፋታ" ዘንድሮ በ"ጊፋታ አጊና" ወይም መስከረም 10 ቀን 2019 ዓ.ም ተወላጆችና የተለያዩ እንግዶች በተገኙበት በደማቅ ሁኔታ ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም