የጊፋታ በዓል እሴቶችን ልማትን ለማሳለጥ ልንጠቀማቸው ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የጊፋታ በዓል እሴቶችን ልማትን ለማሳለጥ ልንጠቀማቸው ይገባል
ሃዋሳ፤ መስከረም 7/2019 (ኢዜአ)፦በአለም ቅርስነት የተመዘገበው የጊፋታ በዓል እሴቶች የህዝቦችን ትስስርና አንድነት ስለሚያጠናክሩ ልማትን ለማሳለጥ ልንጠቀማቸው ይገባል ሲሉ የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ጥራቱ በየነ ገለጹ።
የወላይታ ዘመን መለወጫ "ጊፋታ" በዓል በሐዋሳ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።
ከንቲባ ጥራቱ በየነ በወቅቱ እንደገለጹት፤ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የጊፋታ በዓል እሴቶች የህዝቦችን ትስስርና አንድነት ስለሚያጠናክሩ ልማትን ለማሳለጥ ልንጠቀማቸው ይገባል።
በዓሉ እርቅን፣ አንድነትንና ሰላምን በማብሰር ወደ አዲስ ዕቅድና ተስፋ የሚያሸጋግር መሆኑን ጠቅሰው፤ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስሩን በማጠናከር በአንድነት ድህነትን ማሸነፍ እንደሚገባም ገልጸዋል።
የሲዳማና የወላይታ ሕዝቦች ያላቸውን ጠንካራ ትስስር በሚከናወኑ የልማት ስራዎች ማረጋገጥ እንዳለባቸው የገለጹት ከንቲባው፤ ሀዋሳን የቱሪዝምና የኮንፈረንስ ማዕከል ለማድረግ የተጀመረው ጥረት በሁሉም ተሳትፎ ይጠናከራል ብለዋል።
በዚህም የሀዋሳና የወላይታ ሶዶ ከተሞች ያላቸውን የቱሪዝም ሀብቶች በጋራ በማልማትና በማስተዋወቅ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባም አመልክተዋል።
የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ በበኩላቸው፤ ጊፋታ የዘመን መለወጫ ብቻ ሳይሆን የመተሳሰብንና የአብሮነትን እሴትን በውስጡ የያዘ መሆኑን ገልጸዋል።
በዓሉ የጠበቀ ማኅበራዊ መስተጋብር ያላቸውን የሲዳማና የወላይታ ሕዝቦች አንድነት በሚያጎላ መልኩ በሐዋሳ መከበሩ ትስስራቸውን የሚያጠናክር መሆኑንም ገልጸዋል።
በመሆኑም ሁለቱ ሕዝቦች የጋራ እሴቶቻቸውን በማጠናከር ለሀገረ-መንግሥት ግንባታ ማዋልና መተጋገዝን ማስቀጠል እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል በሐዋሳ የዳዎኤ ቡሹ ወጣቶች ቡድን አባል የሆነው ወጣት እስራኤል ገልፋቶ፤ የጊፋታ በዓል የወላይታና የሲዳማ ሕዝቦችን ወንድማማችነት በሚያጠናክር መልኩ መከበሩን ገልጿል።
ሁለቱን ሕዝቦች የሚያስተሳስሯቸው እሴቶች በርካታ መሆናቸውን ጠቅሶ፤ በዓሉ በሐዋሳ መከበሩም ይህንን ያጠናክረዋል ብሏል።
የሲዳማ ፊቼ ጨምበላላ እና የወላይታ ጊፋታ በዓላት በዓለም ቅርስነት በመመዝገባቸው ወጣቱ እሴቶቹን መጠበቅ እንዳለበትም አሳስቧል።
በወላይታ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የቋንቋና ሥነ-ጥበብ ዳይሬክተርና የበዓሉ ታዳሚ አቶ ፍጹም ዛራ በበኩላቸው፤ የሰላምና የአንድነት በዓል የሆነውን ጊፋታ በጋራ ማክበር የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን ያጠናክራል ብለዋል።
በዓሉ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበና ጠቃሚ እሴቶችን በውስጡ የያዘ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሁላችንንም ጥበቃ ይፈልጋል ብለዋል።
በዓሉ ከሲዳማ ሕዝብ ጋር በሐዋሳ መከበሩም ባህሉን ከማስተዋወቅ ባለፈ በጋራ የልማት እንቅስቃሴዎችን የማየት እድልን የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
በመድረኩም የሀዋሳና የወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች፣ የወላይታና የሲዳማ ሀገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች የተገኙ ሲሆን፤ በጊፋታ በዓል እሴቶች ላይ ያተኮረ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።
በዓሉን የሚያንጸባርቁ የተለያዩ ኪነ-ጥበባዊ ሥራዎችም ቀርበዋል።