ቀጥታ፡

በአትሌቲክሱ ዘርፍ ታሪክ ለመጻፍ ተስፋን የሰነቁ ታዳጊ ስፖርተኞች

የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በየዓመቱ በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች ታዳጊዎችን በማሰልጠን ተተኪ ስፖርተኞችን እያፈራ ይገኛል።

በ2019 በጀት ዓመትም በአትሌቲክስ፣ በእግር ኳስ፣ በቅርጫት ኳስ፣ በቦክስ፣ በፓራሊምፒክ እና በሌሎች የስፖርት ዓይነቶች ታዳጊዎችን ተቀብሎ ለማሰልጠን ነሐሴ 2018 ዓ.ም. በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ የመጀመሪያ ዙር የእጩ ታዳጊ ሰልጣኞች ምልመላ አካሂዷል።

በመጀመሪያው ዙር ከተመለመሉ እጩ ሰልጣኝ ታዳጊዎች መካከል በዘንድሮ ዓመት አካዳሚውን የሚቀላቀሉ ሰልጣኞችን ለመለየት ደግሞ ከመስከረም 5 ቀን 2019 ዓ.ም. ጀምሮ የመጨረሻ የምልመላ እያካሄደ ነው።

የአካዳሚው አሰልጣኞችና ታዳጊ ሰልጣኞች ለኢዜአ እንዳሉት፤ አካዳሚው ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ታዳጊዎች ክህሎታቸውን የሚያሳድጉበት ዕድል በመፍጠር ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው።


 

ከአርሲ በቆጂ የመጣውና የአካዳሚውን የመጨረሻ ዙር ሥልጠና እየተወዳደረ የሚገኘው የ17 ዓመቱ ታዳጊ ዳግም ደጀኔ፤ ለአትሌቲክስ ባለኝ ልዩ ፍቅር ሀገሬን በዓለም አደባባይ ለማስጠራት ሕልም አለኝ ብሏል።

የሥልጠና ምልመላ ሂደቱንም በስኬት ለማለፍ የቴክኒክ፣ የሥነ-ልቦናና ሌሎች ቅድመ ዝግጅቶችን በማድረግ መወዳደሩን አስታውቋል።

ሌላኛዋ የ17 ዓመት ታዳጊዋ ሰሚራ ሸምሱ በበኩሏ፤ በአካዳሚው ምቹ የስፖርት መሠረተ ልማት በመሰልጠን የዕድሉ ተጠቃሚ መሆን በመቻሏ ዝግጁ መሆኗን ገልጻለች።


 

አትሌቲክስ የሀገር ፍቅርን የምናሳይበት መድረክ በመሆኑ ይህን የስፖርት ዓይነት ልመርጥ ችያለሁ ያለው ደግሞ ከጉራጌ ዞን የመጣው የ17 ዓመቱ ታዳጊ ሰለሞን ግርማ ነው።


 

በአትሌቲክስ መስክ የተሻለ ሳይንሳዊ ሥልጠና ወስዶ ስመጥር አትሌት ለመሆን ወደ አካዳሚው መግባት የሚያስችለውን ውድድር በማድረግ የተተኪ ስፖርተኞች አካል ለመሆን መዘጋጀቱን ተናግሯል።


 

የ16 ዓመቷ ታዳጊ ሕንደኬ በሬ በበኩሏ በዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድር መድረኮች የኢትዮጵያን ባንዲራ ከፍ ያደረጉ አትሌቶችን እያየች ማደጓ ለአትሌቲክስ ፍቅር እንዲኖራት እንዳስቻላት ገልጻለች።

የወደፊት ሕልሟ የመሰናክል ሯጭ መሆን እንደሆነ በመግለጽ፣ ለዚህ የስፖርት ዓይነት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ አካዳሚውን ለመቀላቀል ጥረት እያደረገች እንደምትገኝ ጠቁማለች።


 

በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የምርምር ቤተ-ሙከራ ወርክሾፕ ኃላፊ በእምነት ተለሞስ እንዳሉት፣ አካዳሚው ታዳጊዎችን ተቀብሎ ለማሰልጠን የሰልጣኞች መመልመያ መስፈርቶችን አዘጋጅቶ እየተጠቀመ ነው።

ከመስፈርቶቹ መካከልም ታዳጊዎቹ ለእያንዳንዱ የስፖርት ዓይነት የሚገኙበትን የቴክኒክና የአካል ብቃት፣ የታዳጊዎች የጤና ሁኔታና የሥነ-ልቦና ደረጃ ጉዳዮችን መካተታቸውን አብራርተዋል።


 

በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የአትሌቶች ትምህርትና ሥልጠና መሪ ሥራ አስፈፃሚ ኢንስትራክተር ፍቃዱ ከበደ በበኩላቸው፣ በ2019 በዘጠኝ የስፖርት ዓይነቶች ከ16 እስከ 17 ዓመት የዕድሜ ክልል የሚገኙ 358 ታዳጊዎችን ለማሰልጠን መታቀዱን አስታውቀዋል።

የሥልጠና ዓይነቶችም አትሌቲክስ፣ እግር ኳስ፣ ቅርጫት ኳስ፣ ቦክስ፣ ፓራሊምፒክ፣ ቮሊቦል፣ ብስክሌት፣ ወርልድ ቴኳንዶ እና ጠረጴዛ ቴኒስ መሆናቸውን አብራርተዋል።

በዚህም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለመጨረሻ ዙር 638 እጩ ሰልጣኞችን በመመልመል አካዳሚውን የሚቀላቀሉ 358 ታዳጊ ስፖርተኞችን ለመምረጥ የመጨረሻ ዙር ምልመላ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በመጨረሻ ዙር ምልመላ የሚያልፉ ታዳጊዎችም በተመለመሉበት የስፖርት ዓይነት ለአራት ዓመታት በአካዳሚውና በአሰላ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል ሳይንሳዊ ሥልጠና እንደሚከታተሉ ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም