ቀጥታ፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከሕገ-መንግሥታዊ ተልዕኮው ጎን ለጎን ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 7/2019 (ኢዜአ)፦ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከተሰጠው ሕገ-መንግሥታዊ ተልዕኮ ጎን ለጎን ማኅበራዊ ኃላፊነቱን በተግባር እየተወጣ እንደሚገኝ የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።

አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በፌዴሬሽን ምክር ቤትና ተጠሪ ተቋማት በሶማሌ ክልል ጎዴ ከተማ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የተገነቡ መኖሪያ ቤቶችን ለተጠቃሚዎች አስረክበዋል።

አፈ-ጉባኤው በርክክቡ ወቅት እንደገለጹት፤ ምክር ቤቱ አነስተኛ ገቢ ያላቸውንና አቅመ-ደካማ ዜጎችን የመደገፍና የኑሮ ደረጃቸውን የመለወጥ ተግባርን እየሠራ ይገኛል።


 

የለውጡ መንግሥት ዋና የትኩረት አቅጣጫም ልማትን ማፋጠንና ማንንም ያላገለለ የሕብረተሰብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ይህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባር በተለያዩ ክልሎች መከናወኑንና አበረታች ውጤት መመዝገቡን ጠቅሰው፤ የሶማሌ ክልልም ዘርፈ ብዙ የልማት ተግባራት የተከናወኑበትና አሁንም እየተከናወኑበት ያለ ክልል መሆኑን ገልጸዋል።

በዛሬው ዕለት የተላለፉት ቤቶች ሙሉ የቤት ቁሳቁስ የተሟላላቸውና ለተጠቃሚዎችም ለአንድ ወር የሚሆን ቀለብ ጭምር የቀረበላቸው መሆኑን ገልጸዋል።


 

ይህ የቤቶች የርክክብ መርሃ-ግብር የምክር ቤቱን ሕዝባዊ ወገንተኝነት የሚያሳይ መሆኑንና ምክር ቤቱ ከተጠሪ ተቋማት ጋር በመሆን ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የሚያደርጉትን እገዛ በቀጣይም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የሶማሌ ክልል ሴቶችና ሕፃናት ቢሮ ኃላፊ ሐሊማ ሐሰን በበኩላቸው፤ "ዛሬ የደስታ፣ የተስፋና የክብር ቀን ነው" ብለዋል።


 

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ያከናወነው ተግባር መንግሥት የሕዝብን ልማት ለማረጋገጥ ምን ያህል ቁርጠኛ መሆኑን የሚያሳይ ማሳያ በመሆኑ ለምክር ቤቱና ለተጠሪ ተቋማቱ ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል።

የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚዎች በበኩላቸው፤ ቀደም ሲል ይኖሩበት የነበረው ቤት በክረምት ለዝናብ፣ በበጋ ደግሞ ለፀሐይ ያጋልጣቸው እንደነበር አስታውሰዋል።

አሁን ግን የተሰጣቸው ዘመናዊ መኖሪያ ቤት ከዚህ ሁሉ እንግልት እንደታደጋቸው ተናግረው፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤትና ተጠሪ ተቋማት ላደረጉላቸው ድጋፍ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም