የአየር ጠባይ ሁኔታ ትንበያ መረጃዎችን በስፋት ተደራሽ በማድረግ የተሻለ ዝግጁነት እንዲኖር በቅንጅት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአየር ጠባይ ሁኔታ ትንበያ መረጃዎችን በስፋት ተደራሽ በማድረግ የተሻለ ዝግጁነት እንዲኖር በቅንጅት እየተሰራ ነው
አዳማ፤ መስከረም 7/2019(ኢዜአ )፡-የአየር ጠባይ ሁኔታ ትንበያ መረጃዎችን በስፋት ተደራሽ በማድረግ የተሻለ ዝግጁነትና ቅድመ ጥንቃቄ እንዲኖር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ኢንስቲትዩቱ የባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የክረምት ወቅት የአየር ጠባይ ግምገማና የመጪው በጋ ወራት የአየር ጠባይ ሁኔታ ትንበያ መድረክ በአዳማ በማካሄድ ላይ ይገኛል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ(ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለፁት፤ ኢንስቲትዩቱ ለሀገሪቷ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ጠቀሜታ ያላቸውን የአጭርና የረዥም ጊዜ የአየር ፀባይ ትንበያዎችን በወቅቱ በማቅረብ ሚናውን እየተወጣ ይገኛል።
መረጃዎቹ በተለይም ለግብርና፣ ለውሃ ሀብት አስተዳደር፣ ለአደጋ ስጋት ቅነሳ፣ ለአቪየሽንና ትራንስፖርት፣ ለመስኖ ልማት እንዲሁም ለትምህርትና ጤና ዘርፎች እንቅስቃሴዎችን ለማከናወን ቁልፍ አጋዥ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በመሆኑም ወቅታዊና አስተማማኝ የአየር ፀባይ መረጃዎችን ለተጠቃሚው ህብረተሰብና ለባለድርሻ አካላት ተደራሽ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አብራርተዋል።
ወቅቱን የጠበቀና ትክክለኛ የአየር ፀባይ መረጃ ተደራሽነትን ማረጋገጥ ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ልማትና ዕድገት ወሳኝ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
ባለድርሻ አካላትም በየወቅቱ ተደራሽ የሚደረጉ የአየር ፀባይ ሁኔታዎችን በአግባቡ እንዲጠቀሙ በማድረግ ሀገራችን የጀመረችው ልማትና ዕደገት እንዲፋጠን እያደረግን ያለነውን ጥረት አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
መድረኩ የክረምት የአየር ፀባይ ሁኔታን ከመገምገም ባለፈ በመጪው የበጋ ወቅት ሊኖር የሚችለውን የአየር ሁኔታ ትንበያ መረጃን ለተጠቃሚዎች በወቅቱ ተደራሽ በማድረግ ቀድመን ለማዘጋጀትና ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት እንዲቻል መሆኑንም ገልጿል።
የአየር ፀባይ ሁኔታ ትንበያን መሰረት በማድረግ የቅድመ ዝግጅት እርምጃዎችን መውሰድ ከባለድርሻ አካላት ይጠበቃል ያሉት ፈጠነ(ዶ/ር)፤ የአየር ፀባይ ተፅዕኖን ለመቋቋምና ቅድመ እርምጃ ለመውሰድ መድረኩ ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።
የመጪውን የበጋ ወቅት የአየር ፀባይ ሁኔታ ትንበያ ያቀረቡት የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አሳምነው ተሾመ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በመጪው የበጋ ወቅት በአርብቶ አደር አካባቢዎች ለግብርና ልማት ምቹ የሆነ የተሻለ የዝናብ ስርጭት ይኖራል ብለዋል።
በተለይም ምስራቅ ሐረርጌን ጨምሮ የቦረናና ጉጂ ዞኖች፣ ሲዳማና ደቡብ ኢትዮጵያ አከባቢዎች በበጋ ወቅት የተሻለ የዝናብ ስርጭት ያገኛሉ ብለዋል።
አብዛኞቹ የበጋ ወቅት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ዓመታዊ የዝናብ ስርጭታቸውን ከ75 በመቶ በላይ የሚያገኙት በዚህ ወቅት መሆኑን ምክትል ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
ይህም የአየር ፀባይ ተፅዕኖ ለመቋቋምና የውሃ ሀብትን አቅቦ ለመጠቀም ጥሩ አጋጣሚ እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
በዘንድሮው የበጋ ወቅት በኦሮሚያ ክልል በቦረና እና ጉጂ ዞኖች፣ በሶማሌ ክልል ዞኖች፣ እንዲሁም በሲዳማና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች አከባቢዎች ከ75 በመቶ በላይ መደበኛና ከመደበኛ በላይ የዝናብ ስርጭት ይኖራል ተብሎ እንደሚጠበቅም ምክትል ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
የበጋ ወቅት ዝናብ ተጠቃሚ የሆኑ አከባቢዎች ከመጪው ጥቅምት ወር ጀምሮ የዝናብ ስርጭቱን የሚያገኙ መሆናቸውንም ጨምረው ገልጸዋል።