በአማራ ክልል በቀዳማይ ልጅነት እንክብካቤ ጤናማ ሀገር ተረካቢ ዜጋን የማፍራት ቅንጅታዊ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል በቀዳማይ ልጅነት እንክብካቤ ጤናማ ሀገር ተረካቢ ዜጋን የማፍራት ቅንጅታዊ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል
ባህርዳር ፤መስከረም 7/2019 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በቀዳማይ ልጅነት እንክብካቤ ጤናማ ሀገር ተረካቢ ዜጋን የማፍራት ቅንጅታዊ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) ገለጹ።
የማኅበራዊ ክላስተር ተቋማትና ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም የልምድ ልውውጥ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩም ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በቀዳማይ ልጅነት እንክብካቤ ጤናማ ሀገር ተረካቢ ዜጋን የማፍራት ቅንጅታዊ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል።
በዚህም የሕፃናትን የተሟላ እድገትና ጤንነት በማረጋገጥ የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጋን ለማፍራት እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።
ሕፃናትን ተንከባክቦ ማሳደግና በፈጠራ የዳበሩ ማድረግ ሀገርን ለመገንባት ጽኑ መሠረት ማኖር መሆኑንም ገልጸዋል።
ለዚህም የክልሉ መንግሥት ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ ትምህርት ቤቶችን ተደራሽ በማድረግ፣ የምገባ ፕሮግራምን በማጠናከር፣ በተቋማት የሕፃናት መዋያ ቦታዎችን በመገንባትና ሌሎች ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል።
ክልሉ በ25 ዓመቱ አሻጋሪና ስትራቴጂክ ዕቅድ ሕፃናት በአካል፣ በአዕምሮ፣ በሥነ-ልቦናና ግብረ-ገብ ታንጸው እንዲያድጉ ልዩ ትኩረት መስጠቱንም አስረድተዋል።
ይህንን ተግባር ከግብ ለማድረስም ማኅበረሰቡ፣ በሕፃናት ላይ የሚሠሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንዲያጠናክሩ አሳስበዋል።
የአፍሪካ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ማዕከል ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ መሰረት ዘላለም (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ለሕፃናት የተሟላ እድገትና ስብዕና በቀዳማይ ልጅነት ላይ የሚደረገው እንክብካቤ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም በእውቀትና ክህሎት የዳበረ ዜጋን በመፍጠር በተለይም የአፍሪካን እድገት ለማፋጠን ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አስረድተዋል።
የሕፃናት ጉዳይ ለአንድ አካል ብቻ የሚተው ሳይሆን የሁሉንም ትብብር የሚጠይቅ መሆኑን በመገንዘብ፤ ማዕከሉ በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች በሕፃናትና በሰው ሀብት ልማት ላይ በማተኮር እየደገፈ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
የአማራ ክልል መንግሥት ለቀዳማይ ልጅነት እድገት የሰጠው ትኩረት የሚያስመሰግንና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑንም አመልክተዋል።
ለሦስት ቀናት በሚካሄደው በዚህ የልምድ ልውውጥ መድረክ ላይ ከተለያዩ ክልሎች የመጡና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።