ቀጥታ፡

በአፍሪካ ቀንድ ኤልኒኖ ሊያስከትል የሚችለውን የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ለመቋቋም የቀጣናው ሀገራት የቅድመ ማስጠንቀቂያና ቅድመ ትንበያ እርምጃ መውሰድ አለባቸው

‎አዲስ አበባ፤ መስከረም 7/2019 (ኢዜአ):- በአፍሪካ ቀንድ ኢልኒኖ ሊያስከትል የሚችለውን የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ለመቋቋም የቀጣናው ሀገራት የቅድመ ማስጠንቀቂያና ቅድመ ትንበያ እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) አስታወቀ።

ኢጋድ በአፍሪካ ቀንድ ኤልኒኖ የሚያስከትለውን የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ለመቋቋም የቀጣናው ሀገራት የሚያደርጉትን ዝግጅት በተመለከተ በአዲስ አበባ ምክክር እያደረገ ነው።

የኢጋድ ምክትል ዋና ጸሐፊ መሐመድ አብዲ ዋሬ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የኤልኒኖ ክስተት በአፍሪካ ቀንድ በሕይወትና በንብረት ላይ አደጋ ሊያስከትል ይችላል።

በአፍሪካ ቀንድ ከወትሮው የተለየ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ሊያስከትል እንደሚችል የአየር ትንበያ መረጃዎች ያሳያሉ ብለዋል።

የኤልኒኖ መከሰት ተፈጥሯዊ መሆኑን በማንሳት፤ የዝናቡ መጠን በግብርና፣ በእንስሳት እርባታ እና በምግብ ዋስትና ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ጫና መቀነስ እንደሚቻል ገልጸዋል።

ለዚህ ደግሞ ኤልኒኖ በአፍሪካ ቀንድ ሊያስከትለው የሚችለውን የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ለመቋቋም የቀጣናው ሀገራት የቅድመ ማስጠንቀቂያና ቅድመ ትንበያ እርምጃዎችን መውሰድ አለባቸው ብለዋል።

የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎችን ከ24 ሰዓታት በፊት ማድረስ ብቻ የአደጋውን መጠን በ30 በመቶ መቀነስ እንደሚያስችል ገልጸዋል።

ለቅድመ ዝግጅትና ቅድመ ትንበያ እርምጃዎች ፋይናንስ አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ፤ አደጋውን ለመከላከል ከወዲሁ የድጋፍና መልሶ ማቋቋም ወጪን ማሳደግ ይገባል ብለዋል።

የኢጋድ አባል ሀገራት ዕቅዶቻቸውን ማቅረብ፣ ግብዓቶችን አስቀድመው ማከማቸትና ድንበር ተሻጋሪ የማስጠንቀቂያ መረጃዎችን ማጋራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ አጋሮች ኤልኒኖ ሊያስከትለው የሚችለውን አደጋ መከላከል የሚያስችል ድጋፍና አብሮነታቸውን እንዲያሳዩም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም