ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት አስተዳደር ሥርዓት ውስብስብ አደጋዎችን በብቃት ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም እየገነባ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 7/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት አስተዳደር ሥርዓት ውስብስብ አደጋዎችን በብቃት ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም እየገነባ መሆኑን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ።

የምሥራቅ አፍሪካ ልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) በአፍሪካ ቀንድ የኤልኒኖ ዝግጁነት ላይ ያተኮረ ቀጣናዊ ከፍተኛ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው።


 

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ አይድሩስ ሐሰን በዚሁ ወቅት፤ አደጋ ከተከሰተ በኋላ ከሚደረግ ርብርብ ይልቅ በአደጋ ቅድመ መከላከል ትንበያ ላይ ተመሥርቶ የሚወሰድ እርምጃ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በአደጋ ቅድመ ትንበያ፣ በቅድመ መከላከል ዝግጁነትና በቅጽበታዊ የአደጋ ምላሽ አሰጣጥ ውጤታማ የዝግጁነት አቅም በመገንባት ላይ በትኩረት እየሠራች መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም በአደጋ አስተዳደር ሥርዓት ላይ ግንዛቤን በማሳደግ የተለያዩ ዘርፎችንና ባለድርሻ አካላትን ያካተተ የአሠራር ሥርዓት በመቅረጽ እየተተገበረ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ አደጋ ምላሽ ፈንድም ለቅድመ ዝግጅትና ግምገማ የሚሆን ምቹ አቅም በመፍጠር የፋይናንስ ማዕቀፍ እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

የምሥራቅ አፍሪካ ልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) አባል ሀገራትም ከድርጊት በፊት የአደጋ ምላሽ አቅምን የሚያጎለብት የመጠባበቂያ የፋይናንስ አሠራር መዘርጋት እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል።

የቀጣናው ሕዝብ ከትክክለኛ ትንበያ ወደ ሕይወትና ንብረት ጥበቃ የሚያሸጋገር ጠንካራ ምላሽ እንደሚጠብቅ አንስተዋል።

ኢትዮጵያም በራሷ አቅም ምላሽ መስጠት የሚያስችል ጥንካሬ እየገነባች መሆኑንም ተናግረዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ የአደጋ አስተዳደር ሥርዓት ከባህላዊ ምላሽ አሰጣጥ ወደ ቅድመ-ማስጠንቀቂያና አስተማማኝ የመከላከል ሥርዓት መሸጋገሩን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ከኢጋድ፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ከልማት አጋሮችና ከጎረቤት ሀገራት ጋር በመተባበር ቀጣናዊ ኃላፊነቷን ለመወጣት ዝግጁ መሆኗን አስታውሰዋል።

የኤልኒኖ ተጽዕኖዎች ድንበር ተሻጋሪ በመሆናቸው የኢጋድ መድረክ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑንም አመላክተዋል።


 

የኢጋድ ምክትል ዋና ጸሐፊ መሐመድ አብዲ ዋሬ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የኤልኒኖ ክስተት በአፍሪካ ቀንድ በሕይወትና በንብረት ላይ አደጋ ሊያስከትል ይችላል። 

የኤልኒኖ መከሰት ተፈጥሯዊ መሆኑን ያነሱት ምክትል ዋና ጸሐፊው፤ የዝናቡ መጠን በግብርና፣ እንስሳት እርባታ እና ምግብ ዋስትና ላይ ሊያስከትለው የሚችለውን ጫና መቀነስ እንደሚቻል ገልጸዋል።

ለዚህ ደግሞ ኤልኒኖ በአፍሪካ ቀንድ ሊያስከትለው የሚችለውን የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ለመቋቋም የቀጣናው ሀገራት የቅድመ ማስጠንቀቂያና ቅድመ ትንበያ እርምጃዎችን መውሰድ አለባቸው ብለዋል።

የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎችን ከ24 ሰዓታት በፊት ማድረስ ብቻ የአደጋውን መጠን በ30 በመቶ መቀነስ እንደሚያስችል ገልጸዋል።

ለቅድመ ዝግጅትና ቅድመ ትንበያ እርምጃዎች ፋይናንስ አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ፤ አደጋውን ለመከላከል ከወዲሁ የድጋፍና መልሶ ማቋቋም ወጪን ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል። 

የኢጋድ አባል ሀገራት ዕቅዶቻቸውን ማቅረብ፣ ግብዓቶችን አስቀድመው ማከማቸትና ድንበር ተሻጋሪ የማስጠንቀቂያ መረጃዎችን ማጋራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።


 

በተባበሩት መንግሥታት ልማት ፕሮግራም የአፍሪካ ሪዚሊያንስ ማዕከል ዳይሬክተር ዘይኑ ዑመር (ዶ/ር)፤ በኤልኒኖ የሚከሰተውን ተፅዕኖ ለመቋቋም የልማት አጋሮች የፋይናንስ ድጋፍ ማቅረብ አለባቸው ብለዋል።


 

የኤልኒኖን ጉዳት በቅድመ ማስጠንቀቂያ የፋይናንስና የቁሳቁስ ድጋፍ ማጠናከር ይገባል ያሉት ደግሞ በተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት ድርጅት (ዩኒሴፍ) በኢትዮጵያ ተወካይ አቡባካር ካምፖ (ዶ/ር) ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም