ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ማረጋገጥ ብሔራዊ ጥቅም የማስጠበቅና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ጉዳይ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 7/2019  (ኢዜአ):- የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ማስመለስ ብሔራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥና ቀጣናዊ ሰላምን የማጠናከር ጉዳይ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የወጣቶችና ስፖርት አማካሪ ሚኒስትር ቀጀላ መርዳሳ ገለጹ።

የአዲስ አበባ አመራር አካዳሚ የዓባይ ወንዝና የባሕር በር ጉዳይን በተመለከተ የፓናል ውይይት እያካሄደ ይገኛል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የወጣቶችና ስፖርት አማካሪ ሚኒስትር ቀጀላ መርዳሳ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የባሕር በር ከኢትዮጵያ የኢኮኖሚ፣ የጸጥታ፣ የኃይል አቅርቦትና የንግድ ትስስር ጋር የተቆራኘ ነው።


 

ቀይ ባሕር ከዓለም አቀፍ የንግድና የኃይል ማጓጓዣ መስመሮች ጋር የተሳሰረ መሆኑን ገልጸው፤ ለኢትዮጵያ የንግድ ተደራሽነት፣ የሎጂስቲክስ አቅም፣ የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነትና ጸጥታ ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።

ለኢትዮጵያ የባሕር በር ብሔራዊ ጥቅም የማስጠበቅ፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትና የቀጣናውን ሰላም የማረጋገጥ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ የባሕር በር ከኢትዮጵያ ታሪክ፣ ጂኦግራፊ፣ ኢኮኖሚና የጸጥታ ሁኔታ ጋር የተያያዘ ዘላቂ ሀገራዊ አጀንዳ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ጋር ያላት የጂኦግራፊ ቅርበት፣ የሕዝብ ቁጥሯና እያደገ የመጣው ኢኮኖሚ የባሕር በር አስፈላጊነት የጎላ ያደርገዋል ብለዋል።

ከሀገራዊ ጥቅም ባሻገር ከጎረቤትና ከቀሪው የአፍሪካ ሀገራት ብሎም ከዓለም አቀፍ ሥርዓት ጋር የሚኖረውን የኢኮኖሚና የጸጥታ ትስስር ማጤን እንደሚገባ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የባሕር በርን ጉዳይ በሰላማዊና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ፣ በስምምነትና በትብብር መፍትሔ እንዲያገኝ አጥብቃ ትሻለች ብለዋል።

የአዲስ አበባ አመራር አካዳሚ ፕሬዝዳንት ጣሰው ገብሬ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የባሕር በርና የዓባይ ጉዳዮች ከኢትዮጵያና ከአካባቢው የወደፊት የኢኮኖሚ፣ የደህንነትና የትስስር ጥቅሞች አንፃር ተመዝኖ መመራት እንዳለበት ገልጸዋል።

የባሕር በርና የዓባይ ጉዳዮች በውይይት፣ በመተማመን፣ በሕጋዊ ማዕቀፎችና የሁሉንም ሕዝቦች ዘላቂ የጋራ ጥቅም ታሳቢ በማድረግ መመራት አለባቸው ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም