የጅማ መሶብ አንድ ማዕከል ዘመናዊ አሠራር የተገልጋዮችን እንግልትና የጊዜ ብክነት አስቀርቷል - ኢዜአ አማርኛ
የጅማ መሶብ አንድ ማዕከል ዘመናዊ አሠራር የተገልጋዮችን እንግልትና የጊዜ ብክነት አስቀርቷል
ጅማ ፤መሰከረም 7/2019 (ኢዜአ)፡- የጅማ መሶብ አንድ ማዕከል አሠራሩን የዘመነ በማድረጉ ተገልጋዮች እንግልትና የጊዜ ብክነት ሳይገጥማቸው ቀልጣፋ አገልግሎት እያገኙ መሆናቸውን ገለፁ።
የከተማዋ ተገልጋዮች እንደገለጹት፣ በመሶብ የአንድ ማዕከል የሚሰጡ የህዝብ አገልግሎቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከሩ፣ እየዘመኑ እና ቀልጣፋ እየሆኑ መጥተዋል።
ማዕከሉ በርካታ መሥሪያ ቤቶችን በአንድ ጣሪያ ሥር በማስተሳሰሩ፣ ተገልጋዮች ከቢሮ ቢሮ ያጋጥማቸው የነበረውን እንግልት፣ አላስፈላጊ ወጪና የጊዜ ብክነት ማስቀረት ችሏል።
ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ተስፋዬ በቀለ እንደገለጹት፣ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከመጀመሩ በፊት የነበረው ቢሮክራሲያዊ አሰራር ለአላስፈላጊ እንግልትና የጊዜ ብክነት ይዳርግ ነበር።
በአንድ ዓመት ውስጥ አንድን ጉዳይ ለማስፈጸም ከስድስት ወር በላይ ይመላለሱበት የነበረበት ወቅት እንደነበር በማስታወስ፣ የማዕከሉ መቋቋም ያንን ውጣ ውረድ በመቅረፍ ረገድ ትልቅ ለውጥ ማምጣቱን ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም፣ ቀደም ሲል ወደ ማዕከሉ ያልገቡ ተጨማሪ የመንግሥት ሴክተሮች አሁን ላይ ተካተው አገልግሎት መስጠት በመጀመራቸው፣ የማዕከሉ የአሰራር አቅምና የተቀላጠፈ አገልግሎት የመስጠት አቅም ይበልጥ መጠናከሩን ጠቁመዋል።
ወይዘሮ መሬማ መሀመድ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም የአገልግሎት አሰጣጥ ጉዳይ እጅግ ያስጨንቀን ነበር ብለዋል።
በመንግስት ተቋማት ውስጥ የሚታየው ያልተገባ አሰራር ለእንግልትና ንብረት ብክነት ሲዳርገን ቆይቷል ያሉት ወይዘሮ መሬማ፤ ዛሬ ግን ወደ መሶብ አንድ ማዕከል ስንሄድ በፍፁም መተማመንና በደስታ ነው ብለዋል።
የማዕከሉ ሠራተኞች ለባለጉዳይ ትልቅ ትኩረት መስጠታቸው እንዲሁም አገልግሎቱ በቴክኖሎጂ የታገዘና ፈጣን መሆኑ ከምንም በላይ አስደሳች ነው ብለዋል።
አገልግሎቱ በየጊዜው እየዘመነ መጥቷል ያሉት ደግሞ የጅማ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ አለምነሽ ዲኮ ናቸው።
ለሦስት የተለያዩ ጉዳዮች ወደ ማዕከሉ መምጣታቸውንና ሦስቱንም አገልግሎቶች በአንድ ስፍራ አጠናቀው መመለሳቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።
ወጣት ሚፍታ አብዱልቃድር በበኩሉ መሶብ የአንድ ማዕከል ለአቅመ ደካሞችና ለአካል ጉዳተኞች ምቹና አግባብነት ያለው አሠራር መዘርጋቱን ጠቁሞ፣ ያለምንም መጉላላት ገብቶ ተገቢውን አገልግሎት ማግኘት መቻሉን ተናግሯል።
የጅማ መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ሰራተኞች ሊና አብዱለዚዝ እና ሀናን አሙቲ፤ ተገልጋዮች ወደ ተቋሙ ሲመጡ አገልግሎቱን አጠናቀው ለመውጣት ከ10 እስከ 15 ደቂቃ ብቻ እንደሚወስድባቸው ገልጸዋል።
አሠራሩ ዲጂታላይዝ የሆነና ፈጣን በመሆኑ ተገልጋዮች ለእንግልትና ለጊዜ ብክነት እንደማይዳረጉ የጠቀሱት ሠራተኞቹ፤ እያንዳንዱ ሠራተኛ አገልግሎት የሰጠበት ደቂቃ እየተለካ የሚገመገም በመሆኑ ምንም ዓይነት የአገልግሎት ክፍተት አይፈጠርም ብለዋል።
የጅማ መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አብዲ ሰለሞን፤ ማዕከሉ አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት 2018 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን ከ135 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ማስተናገዱን ገልጸዋል።
እንዲሁም በማዕከሉ ይሰጡ የነበሩት አገልግሎቶች ከ135 ወደ 139 የደረሱ ሲሆን፤ ወደ ማዕከሉ የገቡት ሴክተሮች ደግሞ ከ25 ወደ 29 ማደጋቸውን አስረድተዋል።