የገጠር ኮሪደር ልማት ከባዱን የአኗኗር ሁኔታ ቀላልና ዘመናዊ አድርጎልናል- አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
የገጠር ኮሪደር ልማት ከባዱን የአኗኗር ሁኔታ ቀላልና ዘመናዊ አድርጎልናል- አርሶ አደሮች
ሆሳዕና፤ መስከረም 7/2019 (ኢዜአ)፦ የገጠር ኮሪደር ልማት ከባዱን የአኗኗር ሁኔታ ቀላልና ዘመናዊ እንዳደረገላቸው በከምባታ ዞን የአዲሎ ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለፁ።
የገጠር ኮሪደር ልማት የአርሶ አደሩን የመኖሪያ እና የአኗኗር ዘይቤ በማሻሻል በቤተሰብ ደረጃ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የታለመ ሰው ተኮር የልማት እንቅስቃሴ ነው።
ይህ ሰው ተኮር የልማት እንቅስቃሴ የመኖሪያ ቤቶችን መዋቅር ከማዘመኑም ባሻገር የንጹሕ መጠጥ ውኃ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል እና የባዮጋዝ አገልግሎቶችን እስከ አርሶ አደሩ ደጃፍ በማድረስ ዘርፈ ብዙ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎችን እያስገኘ ነው።
በተለይም ቀደም ሲል በጢስና በጨለማ ይታገሉ የነበሩ አባዎራዎችንና እማዎራዎችን የኑሮ ድካም በመቀነስ፣ የቤተሰብን ጤና በመጠበቅ እና ለሕፃናት ትምህርት ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ረገድ እፎይታን አምጥቷል።
በዚህም አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ከመደበኛ እርሻው ባለፈ የጓሮውን ቦታ በዶሮ እርባታ፣ በንብ ማነብ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በወተት ልማት የማበልጸግ ሥራ በመንግሥት ትኩረት ተሰጥቶት እየተተገበረ ይገኛል።
የወረዳው አርሶ አደሮችም የገጠር ኮሪደር ልማቱ ከባዱን የአኗኗር ሁኔታ ቀላልና ዘመናዊ እንዳደረገላቸው ገልጸዋል።
ከተጠቃሚዎቹ መካከል አርሶ አደር ዝናቡ ኑሬ፣ የገጠር ኮሪደር ልማት አኗኗራቸውን ከማዘመን ባለፈ ሕይወታቸውን እንደቀየረው ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም በአንድ ላይ የነበረውን የሰውና የእንስሳት ማደሪያ በመለየት ይስተዋል ለነበረው የጤና ችግር መፍትሄ ሊያገኙ መቻላቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የመብራት ተጠቃሚ መሆን በመቻላቸውም ከጭስ ጋር የተያያዙ የጤና እክሎችን ማስቀረቱንና ልጆቻቸውም የትምህርት ውጤታቸውን በማታ ጥናት ማሻሻላቸውን አብራርተዋል።
በኮሪደሩ ተጠቃሚ የሆኑት ወይዘሮ ፍሬሕይወት ባንዳ በበኩላቸው የገጠር ኮሪደር ልማት በከተሞች የሚታየውን ዘመናዊ የአኗኗር ዘይቤ ወደ ገጠሩ ማህበረሰብ በማቅረብ ከተማን እንዳይናፍቁ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል።
በአካባቢው የመብራት አቅርቦት ባለመኖሩ ኩራዝ ለመጠቀም ይገደዱ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን ግን ባዮጋዝን በመጠቀም መብራትን ጨምሮ ምግብ ማብሰል የሚችሉበት ምቹ ሁኔታመፈጠሩን አስረድተዋል።
እንዲሁም እንቁላልና ወተትን ጨምሮ የተመጣጠነ ምግብ ከጓሯቸው በቅርበት እንዲያገኙና ከቤታቸው ተርፎ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውንም አክለዋል።
የገጠር ኮሪደር ልማት ትግበራው ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ በውስን መሬት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን ሰብሎች አልምተው እንዲጠቀሙ ማስቻሉን የገለጹት ደግሞ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አርሶ አደር ደግነት ሎላሶ ናቸው።
በልማቱ የሚያገኙት ገቢ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማሻሻል መቻላቸውንም አስረድተዋል።
ከዚህ ቀደም ተገቢ ባልሆነ መንገድ የሚያሳልፉትን ጊዜ ጓሯቸውን በማልማትና በተመቻቸላቸው የኤሌክትሪክ ኃይል ከመገናኛ ብዙሃን መረጃዎችን የመከታተል ዕድል እንደተፈጠረላቸውም ገልጸዋል።
የወረዳው የገጠር ኮሪደር ልማት በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መስከረም 28/2018 ዓ.ም ተመርቆ ለአገልግሎት መብቃቱ ይታወሳል።